
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬዎችን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች ያከፋፍላል፡፡
አርሶአደር እንዳለው አያሌው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባንጃ ወረዳ የሠንከሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ አለባበሳቸው እና የፊታቸው ገጽታ የቆሙበት መሬት እንደካሳቸው ፈገግታቸው ያሳብቃል፡፡ በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ያለሙት ቡና ከችግር እያወጣቸው ነው፡፡ ካገኙት ገቢም ሁለት ቤት ገንብተዋል፡፡ ልጆቻቸው ዕውቀት እንዲሸምቱ እያስተማሩ ነው። አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት ከ1ሺህ በላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ሌሎች በእሳቸው መሥመር እንዲገቡም እያስተባበሩ ነው፡፡
ሌላው ከቡና የሚገኝን ጥቅም ያጣጣሙት አርሶ አደር ጌታሁን አምሳሉ ናቸው፡፡ ከቡና ተክል ጋር የተዋወቁት በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡ አሁን ላይም ያረጀውን ቡና አስወግደው በአዲስ ለመተካት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ አዲስ ቡና የመትከል ህልማቸውን ለማሳካት አጠር ያለች ቁምጣቸውን ለብሰው ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ በተከሉት የቡና ችግኝ ውጤታማ በመኾንም በወረዳው ቡናን ተረክቦ ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከተመሠረተው ማኅበር የመቀላቀል ፍላጎታቸውን በአጭር ጊዜ እንደሚያሳኩትም ነው የሚናገሩት፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባንጃ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አምሳሉ አንተነህ በወረዳው 150 ሺህ የቡና እና 140 ሺህ የአፕል ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ አፈጻጸሙ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መኾኑን የተናገሩት ቡድን መሪው ቡና በክላስተር እየተመረተ እና ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መኾኑንም አስታውሰዋል፡፡ ቡድን መሪው አርሶ አደሮች ቡናን መትከል ብቻ ሳይኾን አምርተው ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየሠሩ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ለቀጣይ ዓመት የሚፈላ አንድ ኩንታል ቡና መነስነሱንም ጠቁመዋል፡፡ ሥርጭቱ እስከ ሰኔ 30 /2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቡና፣ ከ604 ሺህ በላይ የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን አንስተዋል፡፡ ችግኞቹ በአርሶ አደሮች ማሣ፣ በተፋሰሶች እና አልፎ አልፎ በወል ማሳዎች የሚተከሉ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያው አወቀ ዘላለም ከ18 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ581 ሺህ 800 በላይ የአቮካዶ ችግኞች በአጭር ጊዜ ምርት እንዲሠጡ መተከላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ችግኞቹ በመንግሥት ችግኝ ጣቢያ፣ በግለሰብ፣ በማኅበራት እና በተቋማት የተፈሉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ እስካሁን ከ36 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ችግኝ የተሸፈነ ሲኾን በ28 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው የቡና ችግኝ ምርት መሥጠት መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡ በክልሉ 21 መሰረታዊ የቡና ማኅበራት ተቋቁመው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ወጥነት ባለው መንገድ ባይኾንም አቮካዶ ለውጭ ገበያ እየቀረበ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ለሚተከሉ ችግኞች ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!