“ጠፍጣፋ ድንጋይ መሮ አይበሳውም፣ የአባቱን ታሪክ ልጁ አይረሳውም”

106

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጀግና ልጆች ታሪካቸውን አይረሱም፣ ቃል ኪዳናቸውን አያጥፉም፣ ማሕተባቸውን አይፈቱም፡፡ የጀግና ልጆች የአባትና የእናታቸውን አይጥሉም፣ ታሪካቸውን ያስታውሳሉ፣ ታሪካቸውን ያስጠብቃሉ፣ ያስከብራሉ፡፡ ታሪክም ይሠራሉ፡፡

የወልቃይት ጀግኖች፣ የጠገዴ አንበሶች፣ የበረሃዎቹ መብረቆች “ ሞት አይቀርም ስም አይቀበርም” ይላሉ፡፡ ከመቃብር በላይ ለሚቀረው ስማቸው፣ ትውልድ ለሚያነሳው ዝናቸው፣ በወርቅ ብራና ላይ ለሚሰፍረው፣ ሲዘከር ለሚኖረው ታሪካቸው፣ ከአባት እናት ለወረሱት ቃል ኪዳናቸው ያላቸውን ክብር ሲናገሩ፡፡ እነርሱ የማይቀረው ሞት አያስፈራቸውም፣ የሞት ንውጽውጽታ፣ ውሽንፍርና ፍላጻ አያስደነግጣቸውም፣ ከሞት በላይ መልካም ታሪክ መሥራት ያሳስባቸዋል፡፡ መልካም ታሪክ ጽፈው ለማለፍ ይታትራሉ፤ ሞትን ይንቃሉ፡፡

“ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከሞት” እንዳሉ ሞትማ አይቀርም፡፡ ሁሉም ያልፋል፤ ሁሉም ነበር ይባላል፡፡ ሞት የማይገድለው፣ ዘመን የማይሽረው ፣ የመቃብር ድንጋይ የማይጫነው ስም ግን ከመቃብር በላይ ይውላል፡፡
አበው መልካም ስምን ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር፣ አባት የሰጠው ወንበር ይሉታል፡፡ መልካም ስምና መልካም ሥራ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ትናንትን አልፎ ዛሬ ላይ ይደርሳል፣ ዛሬን አሳልፎ ለነገ ይቆያል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጀግኖችም ለዚህ ነው ሞት አይቀርም ስም አይቀበርም የሚሉት፡፡

በዚያ ምድር ፈሪ አይኖርም፣ ዋሾና አታላይ ውሎ አያድርም፡፡ ሰላቶ አይረማመድም፡፡ በዚያ ምድር እውነት፣ ጀግንነት፣ ጽናት፣ ትዕግሥት እና አርቆ አሳቢነት ሞልቷል፡፡ ልቡን ያመነ ጀግና ይወለድበታል፣ በጀግንነት ያድግበታል፣ በጀግንነት ይኖርባታል፣ የጀግንነት ታሪክም ይሠራበታል፡፡ እንኳን ሰዎቹ የሚያርሷቸው በሬዎች፣ የሚያልቧቸው ላሞች በዋዛ አይቀመሱም፣ በአንድነት እየተጓዙ የሚነካቸውን ያስበረግጋሉ፣ የሚደፍራቸውን ያሸሻሉ እንጂ፡፡

የእነርሱን ጀግንነት፣ የእነርሱን ጽናት ተከዜ አንደበት ቢኖረው ይመሰክራል፣ ተራራዎች አንደበት ቢሰጣቸው ይናገራሉ፣ ለዘመናት ያዩትን እውነትና ጀግንነት፣ ትዕግስትና ጽናት ለጠየቃቸው ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡

በግመሎቻቸው፣ በአጋሰሶቻቸው ወርቅና ዝባዱን፣ ብርና አልማዙን የከበረ ማዕድኑን ጭነው ረጅም መንገድ የሚጓዙት የሲራራ ነጋዴዎች ከቀይ ባሕር ተጉዘው፣ የኤርትራን አውራጃዎች አቆራርጠው፣ በእምነሃጅር አልፈው፣ ተከዜን ተሻግረው ሁመራ የጎንደርን ምድር ይረግጣሉ፡፡

በተከዜ ዳሯ እመቤት አርፈው፣ ከወተትና ከማሩ ተጎንጭተው፣ ግመሎቻቸውን አስነስተው፣ ወደ መናገሻዋ ይጓዛሉ፡፡ በመናገሻዋ ከተማም ይከትማሉ፡፡

የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በሁመራ ሃምዳይት አቅጣጫ ጀምሮ እስክ መተማና ቋራ ከዚያም እያለፈ ከሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ ከሱዳን የሚነሱ ነጋዴዎች እና ሀገር አሳሾችም በዚሁ ወሰን ይገባሉ፡፡ ሁመራ ደግሞ የብዙ ነጋዴዎች መገናኛ ነበረች፡፡ እነዚያ የበረሃ አናብስት የወልቃይት ጠገዴ ጀግኖችም ወተትና ማሩን፣ ቅቤና ቅመሙን፣ ማሽላና ሰሊጡን፣ በቆሎና ጥጡን እየጫኑ ወደ መናገሻቸው ጎንደር ይገሰግሳሉ፡፡ በመናገሻዋ ጎንደርም በደረሱ ጊዜ ያሻቸውን እያደረጉ በከተማቸው ይሰነብታሉ፡፡ እንዲህ እየሆነ ትውልድ አልፎ ትውልድ እየተተካ፣ ታሪክ እየተሠራ፣ ለልጅ ልጅ እየተነገረ፣ ልጅና የልጅ ልጅም የራሱን ታሪክ እየሠራ ዘመናት ነጎዱ፡፡

የወልቃይት ጎበዛዝት ነጭ ኩታቸውን ለብሰው፣ ያማረ ባርኔጣቸውን ደፍተው፣ ቀይ ከዘራቸውን እንዲያም ሲል ከትራሳቸው የማትጠፋውን መሳሪያቸውን ይዘው ከቤት ሲወጡ አጀብ ያሰኛሉ፡፡ የልባቸው ኩራት፣ አረማመዳቸው ሁሉ ያያቸውን ያፈዝዛሉ፡፡ ወይዛዝርቱ የተዋቡን ቀሚስ ይለብሳሉ፣ በማረው ወገባቸው ላይ ውብ የሆነውን መቀነት ሸብ ያደርጋሉ፣ ድሪና ብርቅጥሉን በመቃ አንገታቸው ላይ ያሥራሉ፣ በአንባርና በአልቦው እንደ ወግና ስርዓቱ እንደ ባሕሉ ያጌጣሉ፣ በአንገታቸው አልፎ በጀርባቸው የሚገማሸረውን ጸጉራቸውን ሹርባ ይሠራሉ፡፡ ያን ጊዜ ውበት በእግሩ ሲራመድ ይታያል፣ ደም ግባት በሰው ፊት ሁሉ ይመላለሳል፡፡

በአባቶቻቸው ቤተ መንግሥት ከሚኖሩት ልዕልቶች ውጭ አምሳያ ሌላ አምሳያ የላቸውም፣ ባሕላቸውና ወጋቸው፣ ቋንቋቸውና ማንነታቸው አንድ የሆነው ከጎንደር ወይዛዝርት፣ ከጎንደር ልእልት ጋር ነው፡፡
ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር አብራክ፣ መናገሻው ጎንደር፣ ማንነቱ አማራ፣ ወንዙ ተከዜ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ያለ ያለ ማንነቱ ማንነት፣ ያለ ባሕሉ ባሕል ሊጭኑበት ተነሱበት፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጀግና ግን አይደረግም አለ፡፡ ለዓመታት በደል ፈጸሙበት ከማንነት እና ከእውነት ግን ሸብረክ ሳይል ኖረ፡፡ የጠላቶቹን ክንድም ሰበረ፡፡ ነጻነቱን እና ማንነቱንም አስከበረ፡፡

ገሪማ ታፈረ የስሜን በጌምድርን አርበኛች ተጋድሎ በጻፉበት “ጎንደሬ በጋሻው” መጽሐፋቸው ጀግኖች አርበኞች እንደሌሎቹ የስሜን በጌ ምድር ወረዳዎች በወልቃይት ጠላትን ለመደምሰስ ጀግኖች አርበኞች ዘመቱ፡፡ ጦሩ በጀግኖች አርበኞች ደጅ አዝማች ሐጎስ ተሰማ፣ ደጅ አዝማች ብሬ ዘገየ፣ ደጀአዝማች አዳነ መኮንን (ቢትወደድ) ፣ ደጅአዝማች ደስታ ማሩ፣ ፊታውራሪ መስፈን ረዳ፣ ደጅአዝማች አያናዬ ቸኮል እየተመራ የኢጣልያን ጦር ዘመተበት፡፡ በዚሕ ጦርነት የጠላትን ሠራዊት ሬሳ በሬሳ አድርጎ ድል መታው፡፡ ከድል በኋላም ፊታውራሪ መስፍን ረዳ ወልቃይትን እንዲያስተዳድሩ ተደረገ ብለዋል፡፡

እሳቸው ታሪክ የጻፉት የስሜን በጌምድርን አርበኞች እና በስሜን በጌምድር ከጠላት ጋር የተደረጉ ጦርነቶችን ነው፡፡ ወልቃይት ጠገዴም የስሜን በጌምድር አብራክ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡

ወልቃይት በዚያ ዘመንም፣ ከዚያ ዘመንም አስቀድሞ፣ ከዚያም በኋላ የጎንደር አብራክ ነው፡፡ የስሜን በጌምድር በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ በኩል በቀድሞ በኤርትራ ክፍለ ሀገር በአሁኑ ከሀገረ ኤርትራ፣ ከሡዳን ተከዜን አልፎም በትግራይ ክፍለ ሀገር ጋር የሚዋሰን አካባቢ ነው፡፡ የበረሃው ውብ ስፍራ፣ የተከዜ ዳሯ መልካም ምድር የስሜን በጌምድሯ ሁመራ ከተማ ከኤርትራ፣ ከትግራይ፣ ከሱዳን እና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች መገናኛ ናት፡፡

ጀብደኛው ጦረኛ ራስ አሞራው ውብነህም በኢጣልያ ወረራ ወቅት አስመራ የሠፈረው የኢጣልያ ሠራዊት በሁመራ ተሻግሮ የጎንደርን መሬት እንዳይረግጥ እየጠበኩ አስመራን ለማስለቀቅ አሳብ አድርጌ በሱዳን ወሰን ያለውን በረሃማ በቁጥጥሬ ሥር አደረኩ ብለዋል ስለ እርሳቸው በሚዘክረው መጽሐፋቸው፡፡

“ጠፍጣፋ ድንጋይ መሮ አይበሳውም

የአባቱን ታሪክ ልጁ አይረሳውም” እንዲሉ አበው ወልቃይት ጠገዴን ከተከዜ ማዶ ተሻግረው የመጡ ታጣቂዎች የእኛ ይሁን ቢሉም ልጆች የልጅ ልጆች የአባታቸውን ታሪክ እያነሱ፣ ማንነታቸውን እየነገሩ አይሆንም ብለዋቸው ኖሩ፡፡
“ጠፍጣፋ ድንጋይ አይቆረስም

ጀግናው ለጠላት አይቀመስም” እንደተባለ በታሪክ ሆኖና ተደርጎ የማያውቀውን ለማድረግ የመጡትን ታጣቂዎች ጀግኖቹ አንቀመስም ብለው ተዋጓቸው፡፡ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ታገሏቸው፡፡ በጻና ትግላቸውም እውነታቸው እና ማንነታቸውን አጸኑ፡፡ ተወልደው ባደጉበት ታሪክ በሠሩበት ምድራቸውም ኖሩ፡፡ የእነዚያ ጀግኖች ልጆች ታሪካቸውን እያስታወሱ፣ ታሪካቸውን እያወሱ፣ ለጠላት ሳይቀመሱ ኖረዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴው ሰቲት ሁመራ ተወላጁ እና በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ትግል ላይ ሲታገሉ የኖሩት አታላይ ዛፌ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሥር ሲተዳደር የኖረ፣ ከጎንደር ሕዝብ ተነጥሎ የማያውቅ፣ ሊነጠል የማይችል ነው ይላሉ፡፡ ወልቃይት የእኛ መሆን አለበት ያሉ ዘመነኞች ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር አማራ ለመነጠል ቢያስቡም ስጋና ደምን መለያየት አልተቻልም፣ አይቻልምም ነው የሚሉት፡፡ በአፈሙዝ ያለ ማንነቱ ማንነት ለመስጠት ለዓመታት ቢጥሩም የአባቱን ታሪክ እና ማንነት የማይረሳው ጀግናው ሕዝብ ግን አሻፈረኝ ብሎ ኖረ፡፡

የወልቃይት ሕዝብ እስክስታው፣ ጭፈራው፣ የለቅሶ ስርዓቱ ሁሉም የጎንደር አማራ እንጂ የሌላ አይደለም፣ የጠረፍ ሰው ስለሆነ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገራል፣ ከሡዳናውያን ጋር ስለሚገናኝ አረብኛ፣ ከኤትራውያን እና ከትግራይ ጋር ስሚገናኝ ትግርኛን ከራሱ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር ደርቦ ይናገራል፣ ነገር ግን ማንነቱ እና ግዛቱ የስሜን በጌምድር እንጂ፣ ከተከዜ ተሻግሮ ወደ ትግራይ ተካሎ አያውቅም፣ ከተከዜ ማዶ የመጣ ሰውም አስተዳድሮት አያውቅም ብለውኛል፡፡

የወልቃይት ጀግኖች በአባቶቻቸው ባድማ እያረሱና እያፈሱ ሀገር ሲጠብቁ ኖረዋል፣ በሀገር ላይ የተነሳን ጠላት እየቀጡ ሠንደቅ አስከብረዋል፡፡ ደጅ አዝማቾች፣ ፊታውራሪዎች፣ ራሶች፣ ልበ ሙሉ ጀግኖች የሚወለዱበት ምድር ለጠላት አይቀመስም፡፡ ሀገሩን ይወዳል፣ ሠንደቁን ያስከብራል፣ ያከብራል፣ ለማንነቱ ግንባሩን ይሰጣል፡፡ እንዲህ ሲያደርግ እና ሲቀባበል ነው የኖረው፡፡

በአባትና እናቶቻቸው መሬት በትራክተር እያረሱ፣ እያፈሱ ከራሳቸው አልፈው ለሀገሩ ይተርፉ ነበር፡፡ በቀደመው ዘመን ለእርሻ ልማት እና ለሌሎች ከውጭ የሚመጡ ጥሬ እቃዎች በቀይ ባህር ኤርትራ ተሻግረው በዚያኔው የኤርትራ ክፍለ ሀገር በዛሬው ሀገረ ኤርትራ አድርገው ስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሁመራ ያመጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ የልማት እና የጦር አርበኞች የኖሩበት፣ ባላባቶች የመሉበት ምድር ነው ወልቃይት፡፡ ወልቃይት የእኛ ትሁን የሚሉት ሁሉ የወልቃይትን እውነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ እውነታውን ግን መቀበል አይፈልጉም ብለውኛል፡፡ የወልቃይትን እውነት እና ማንነት መቀበል ግድ ይላልም ነው ያሉኝ፡፡ ተከዜ የስሜን በጌምድር እና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት የሚዋሰኑበት ሕያው ምስክር ሆኖ ኖሯል፡፡

በአንድ ወቅት የትግራይ ነጻ አውጭ ነን የሚሉ ሰዎች ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ወስደን ወደ ትግራይ አካለነዋል ያሏቸው አዛውንት ተከዜንስ የት አደረሳችሁት? አሉ ይባላል፡፡ ተከዜ ሕያው ምስክር ነው፣ ተከዜን በሌላ ሀገር እንዲፈስስ ካላደረጋችሁት የጎንደርን እና የትግራይን ድንበር ማጥፋት አትችሉም፣ የትግራይ ግዛት ከተከዜ ተሻግሮ አያውቅም፣ ዛሬ ቢመስላችሁ ነገ ወደ እውነቱ መመለሱ አይቀርም አሉ ይባላል፡፡ ወልቃይትን የሚፈልጉት መሬቱን፣ ሃብቱን ነበርና የወልቃይትን ባላባት ጨፈጨፉ፡፡ እልፍ በደልም ፈጸሙ፡፡

ከትግራይ ተከዜን ተሻግረው ለሥራ ወደ ወልቃይት የሚመጡ ሀብት አፍርተው፣ መልካም ጊዜ አሳልፈው፣ ሲመለሱም ስንቅ ተቋጥሮላቸው፣ ሸኚ ተዘጋጅቶላቸው ይመለሳሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የራበውን እያጎረሰ፣ የታረዘውን እያለበሰ፣ የጠማውን እያጠጣ ኖሮ ሳለ ወርቅ ላበደረ ጠጠር ተመልሶለት ማንነቱን እንዲጥል፣ የአባቶቹን ታሪክ እንዲተው ለማድረግ ተፈርዶበት እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ቁጥር ስፍር የሌለው በደልም ፈጽመውበታል፡፡ ዳሩ አጠፋነው ያሉት ዘርና ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ እያነሳ፣ እውነቱን እየገለጠ ታገላቸው፡፡ ድልም መታቸው፡፡ ስለ ምን ከተባለ እውነትን ይዟልና፡፡

ባለታሪኮችን፣ ባላባቶችን እናጠፋቸዋለን፣ እንቀብራቸዋለን አሉ፡፡ የአባቱን ታሪክ የማይረሳው፣ የአባቱን ነፍጥ የሚያነሳው ትውልድ ግን አልቀመስ አለ፡፡ ወልቃይት የማንም ሆኖ አያውቅም፣ ወልቃይት የጎንደር አብራክ የጎንደር አማራ ነው፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ በጀግንነት አሸንፏል፣ ሰበርነው ሲሉ ይባስ ጠንክሮ ነጻነቱን አስከብሯል ነው ያሉኝ፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ታሪክ እየጠቀሰ፣ እውነት እየገለጠ ለወዳጀቹም ለጠላቶቹም፣ ለዓለሙ ሁሉ “አማራ ነን እንጂ፣ አማራ እንሁን አላልንም፣ የማይገበንን አልፈን አልጠየቅንም፣ የራሳችንም አሳልፈን አንሰጥም” እያለ በአደባባይ ይናገራል፡፡ ይሄም እውነት ይታወቅለት ዘንድ ታሪክ እየገለጠ ያሳያል፡፡ ወልቃይት ዘመን የማይሽረው እውነት፣ መከራ የማይሰብረው ጽናት፣ ጠላት የማይደፍረው ጀግንነት ያለበት ምድር፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመጀመሪያ ጊዜ በአዊኛ ቋንቋ የተሠራው “አንታጉ” ፊልም ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡
Next articleቡናን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡