በአማራ ክልል የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን በስፋት በማጥናት ዘርፉን ሁነኛ የሃብት ምንጭ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።

81

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል እምቅ የግንባታ እና የከበሩ ማዕድናት ባለቤት እንደኾነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ማዕድናትን ጥቅም ላይ ለማዋል ግን በቅድሚያ የማዕድናቱን ዓይነት፣ መጠን እና የጥራት ደረጃ መለየት አስፈላጊ ነው። የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ሀይሌ አበበ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን በስፋት በማጥናት ዘርፉን ሁነኛ የሥራ እድል መፍጠሪያ እና የሃብት ምንጭ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የማዕድን ሃብት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እስከ ወረዳ እና ቀበሌዎች የሚደርስ መዋቅር ተዘርግቶለት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ቢሮው በዚህ ዓመት 19 ሺህ 175 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለግንባታ የሚውሉ ማዕድናት ጥናት አከናውኗል።

በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ወደ 427 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጥናት በማካሄድ ብረት፣ ኒኬል፣ ሊትየም እና የመሳሰሉ ማዕድናትን ማግኘት መቻሉን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በአማራ ክልል ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩት ማዕድናት 2 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አቶ ሀይሌ አበበ ገልጸዋል። ይህ ገቢ የተገኘው ወርቅ እና ኦፓልን ከመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናት ነው።

አቶ ሀይሌ በአማራ ክልል በርካታ የወርቅ ማዕድን ቢኖርም ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል ብለዋል። በዚህ ዓመት ግን በወርቅ ማዕድን ላይ በትኩረት በመሠራቱ አበረታች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት። በበጀት ዓመቱ 84 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።

ቢሮ ኀላፊው ዜጎች ከባሕላዊ መንገድ እስከ ካምፓኒዎች ደረጃ በማዕድን ሥራ ላይ ተሰማርተው የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው መደረጉንም ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓትም በክልሉ ከ32 ሺህ በላይ ዜጎች በዘርፉ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

በማዕድን ሃብት ዘርፍ ከዚህ በላይ ሥራዎችን በማከናወን ሰፊ ሃብት ለመፍጠር ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲይዝ እየተደረገ ስለመኾኑም አቶ ሀይሌ ገልጸዋል። ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የካርታ ሥራ እና ጥናት ለማከናወን ቢሮው የመግባቢያ ሰነድ እንደተፈራረመም አንስተዋል። በማዕድን ዘርፍ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸውን ምሁራን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት ቢሮው በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ሽዋ ዞን ስድስት ወረዳዎች ሁሉን አውዳሚ ተምች መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
Next articleለመጀመሪያ ጊዜ በአዊኛ ቋንቋ የተሠራው “አንታጉ” ፊልም ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡