
በቀን ወቅያኖስ በማታ ሰደድ እሳት ትመስላለች፡፡
ከመልካሟ ምድር፤ አየሁ ብዙ ሚስጥር
ከመዲናዋ ስር አለ ብዙ ሚስጥር፡፡ ከስሯ ያልተጠለለ የለም፤ የብዙ ብዙ የሆነ ሀብት፣ ያጣ የነጣ ድህነት፣ በድሎት ሽሮ የማይጎርስ፤ በማጣት እህል ውኃ የማይቀምስ፤ ኢትዮጵያዊነትን ወደኋላ የተወ ዘመናዊ፤ ዘመናዊነት ፈጽሞ ያልገባው ባሕላዊ፤ ብቻ ሁሉም በየዓይነቱ ይገኝበታል፡፡ በስሯ ኢትዮጵያዊነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ዘመናዊነትንና ባሕላዊነትን፣ ስለሰው ማሰብንና ሌሎችንም በአንድ ጥላ ስር ተመልክቻለሁ፡፡ የብዙ ብዙ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች መገናኛ እና መከተሚያ ስፍራ ናት፡፡ ነጭና ጥቁር፣ ሀብታም እና ደሀ ታናሽና ታላቅ በጋራ ይኖሩባታል፡፡
ከእንጦጦ ግርጌ እንደፀሐይ ከደመቀችው ከተማ አስደናቂ ነገሮች አሉ፡፡ ከእንጦጦ ተራራ ሰገነት ላይ ሆነው ቁልቁል ሲመለከቷት በቀን ወቅያኖስ በማታ ደግሞ ሰደድ እሳት ትመስላለች፤ አዲስ አበባ፡፡ አዲስ አበባን እንዳዬሁ ‹የአፍሪካውያን ኩራት እምዬ ምኒልክ፤ አንቺ ጀግናና ቆራጥ ንግሥተ ነገሥታት ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ጣይቱ ሆይ አፈሩ ይቀለላችሁ› ስል ፈጣሪን ተማጸንኩ፡፡ የእነዚያ ጀግኖች መሠረት ባይጣልባት ኖሮ ምን አልባትም የዛሬይቱን አዲስ አበባን ማዬት ባልቻልን ነበር፡፡
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን ብዙኃነታቸውን የሚመለከቱባት የሚያስመለክቱባት ሙዚዬማቸውም ናት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ንፍቀ ክበብ ያሉ ኢትዮጵያውያንን እስከነባሕላቸውና ወጋቸው ማግኜት ይቻላል፡፡
አዲስ አበባ እንደ አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ ረጅምድ እድሜ ባይኖራትም ከሌሎቹ የተለዬ እድገት ላይ ናት፡፡ የተመሠረተችው በእምዬ ምኒልክ ዘመን በ1878ዓ.ም እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ የአዲስ አበባን እድሜ ያደለው አንድ ሰው ሊኖረው ይችላል!
እምዬ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን ከሸዋ አንኮበር ወደ እንጦጦ አዘዋውረው ግዛታቸውም ሰፍቶ ነበር፡፡ ከእንጦጦ ሰገነት ላይ ተቀምጠው በመኳንንትና በመሳፍንት ታጅበው አፍሪካን ለማኩራት እያሰቡ በአራቱም አቅጣጫ የተንጣለለውን ሜዳ ወደታች ይመለከቱ ነበር፡፡ በተለይም ከእንጦጦ በስተደቡብ በኩል ያለው ሜዳ ለታላቋ ንግሥተ ነገሥታት ጣይቱ ይስባቸው ነበር አሉ፡፡ ከዕለታት በአንዷ ቀን እምዬ ምኒልክ የሀገራቸውን የምሥራቁን አካባቢ ጦር ለማጠናከርና ሕዝቡንም ለመጎብኜት ወደ ምሥራቅ አመሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ በእንጦጦ ቤተ መንግሥታቸው ከአጋፋሪዎቻቸውና ከአገልጋዮቻቸው ጋር ቀሩ፡፡ ጣይቱ ማለዳ ማለዳ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እጅ እየነሱ ውዳሴ እያቀረቡ ጀንበር ዘቅዘቅ ስትል ደግሞ በክብር ወንበራቸው ተቀምጠው አዲሲቷን ምድር ይመለከቱ ነበርም ይባላል፡፡
አንድ ቀንም ወደዚያች ውብና አዲስ ምድር ወረዱ፤ የተለዬች አበባም አዩ፡፡ ‹‹ይችስ እስካሁን ካየሁት ሁሉ የተለዬች አዲስ አበባ ናት›› አሉ ይባላል፡፡ አካባቢውንም በዚያው አዲስ አበባ አሉት፤ ከተማም እንዲከተም አዘዙ፡፡ ከተማዋ ተቆረቆረች፤ ቤተ መንግሥቱም ወደ አዲሷ ከተማ ወረደ፡፡ አራት ኪሎ ላይ ታላቁ ቤተ መንግሥትም ተሠራ፡፡ እነሆ ቤተ መንግሥቱ ነገሥታትንም፣ ፕሬዝዳንቶችንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችንም አስተናግዷል፤ እያስተናገደም ነው፡፡ በዚያ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኢትዮጵያ ተሠርታም ፈርሳም ታውቃለች፤ አሁንም እጣ ፋንታዋ በዚያ ቤተ መንግሥት ይወሰናል፡፡
በዚያ ዘመን ዘመኑን የዋጀ ቤተ መንግሥት፣ ለኢትዮጵያውያን አዲስ የሆነ ሆቴል እና ሌሎች ቤቶች ከመሠራታቸው በስተቀር ያበበች አዲስ አበባ አልነበረችም፤ ለምን ቢሉ እየተወደለች ነበርና ነው፡፡ አዲስ አበባ ከዓድዋ ድል ማግሥት ኢትዮጵያውያን በጋራ ደስታቸውን ያከበሩባት፣ የንጉሡ አሽከሮች እንቢልታና መለከት እየነፉ ሕዝብ የጠሩባት፣ የደስታ ነጋሪት የጎሰሙባት፣ የጣሊያን ውርደት ሻማ የበራበት፣ የኢትዮጵያ ቀንዲል ከፍ ያለባት ታሪካዊት ምድር ናት፡፡
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እምዬ እንዳስተከሏቸው የሚነገርላቸው ጥንታዊ ዛፎች ይገኛሉ፡፡ የእርሳቸው መታሰቢያ ሃውልትም ፊቱን ወደ ዓድዋ ዞሮ ፈረሳቸው ላይ እንዳሉ በኩራት ቆሟል፡፡ የአዲስ አበባ ወላጆች እምዬና እቴጌ ሲያልፉም የእነርሱን እግር ተከትለው የመጡ ነገሥታት ልጅ እያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ ፣ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ግርማዊ ቀደማዉ ዓፄ ኃይለሥላሴ) ማዕከል አድረገው ኢትዮጵያን አስተዳድረውባታል፤ አዲስ አበባ፡፡
ዘመነ ንግሥና ተሽሮ ዘመነ ፕሬዝዳንትነት ሲመጣ ደግሞ ከፕሬዝዳንት፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም እስከ ፕሬዝዳንት መለስ ዜናዊ ሀገር የመሩት ከእምዬ ቤት ሆነው ነው፡፡ ሀገሪቱ ከፕሬዝዳንታዊ ወደ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ስትሸጋገርም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በእምዬ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሆነው ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በእምዬ ምኒሊክ ግቢ ሆነው ኢትዮጵያን እየመሩ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ የቤተ መንግሥቱ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከቤተ መንግሥቱ የሚመጣውን መልዕክት እንጅ በውስጡ ምን ያህል ሕንጻ እንዳለ እንኳ አያውቁም ነበር፡፡ ግቢው ለብዙዎቻን መገለጥ የጀመረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዘመን ‹አንድነት ፓርክ› ተሠርቶ ለሕዝብ ክፍት ሲሆን ነው፤ ለዚያውም በከፊል፡፡ ቤተ መንግሥቱ የተሻለ ዕድሳት ያገኘውም በዚሁ ዘመን ነው፡፡
በቀደመው ዘመን ጠጅና ማር እንደ እንደ ጎርፍ ተንቆርቁሮበታል አሉ፤ ብዙ ደስታና ፌሽታ ታልፎበታል፤ ቤተ መንግሥቱ፡፡ አዲስ አበባም ቤተ መንግሥቱም የኢትዮጵያ ደስታና መከራ ተፈራርቆባቸዋል፡፡ እነ አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ በርካታ ድንቅ ኢትዮጵያውያን በግፍ ተገድለውባታል፡፡ በሞሶሎኒ የተመራው የፋሽሽት ጣልያን ወታደር ብዙ በደሎችን ፈጽሞበታል፡፡ ጣልያን በኢትዮጵያ በቆየባቸው አምስት ዓመታት የጣሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ዋና አዛዥ መቀመጫም እንደነበረች ይነገርላታል፤ አዲስ አበባ፡፡ ጣሊያን ሁለተኛ ውርደት በዓለም አደባባይ ሲከናነብም በዚችው ከተማ የደስታ ድግስ ተደግሶባታል፡፡
አዲስ አበባ በችግር ውስጥም ሆና የጎልማሳ እድሜ አለፍ ስትል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ ለመሆን በቃች፡፡ በርካታ ዲፕሎማቶችም ሊቀመጡባት ወደዱ፤ ተቀመጡባትም፡፡ አዲስ አበባ ታሪካዊ የሆኑ ስያሜዎች ያሉባት ከተማም ናት፡፡ በተለይም በተመሠረተችበት ዘመን የነበሩ መኳንንት፣ መሳፍንት እና የጦር አበጋዞች ብዙውን የአካባቢ ስያሜ ወስደዋል፡፡ በዚህ መልኩ ስያሜያቸውን ካገኙት ሠፈሮች መካከል ራስ መኮንን ሠፈር፣ ራስ ተሰማ ሠፈር፣ ራስ ብሩ ሠፈር፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ራስ ስዩም ሠፈር፣ ደጃዝማች ውቤ ሠፈር፣ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ደጃዝማች ዘውዱ አባኮራን ሠፈር እና ሸጎሌ ሠፈር ይጠቀሳሉ።
ከእነዚህ ሠፈሮች መካከል ደጃዝማች ውቤ ሠፈር በተለይ ከጣሊያን ወረራ በፊት በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙባቸው የከተማዋ ሠፈሮች አንዱ እንደነበረ ይነገራል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ግጥሞች በዚህ ሠፈር ዙሪያ ተገጥመዋል፤ ከነዚህም መካከል፡-
«ደጃች ውቤ ሠፈር ምን ሠፈር ሆነች፣
ያችም ልጅ አገባች ያችም ልጅ ታጨች።
ደጃች ውቤ ሠፈር ሲጣሉ እወዳለሁ፣
ገላጋይ መስዬ ገሊትን አያለሁ።
ደጃች ውቤ ሠፈር የሚሠራው ሥራ፣
ጠይሟን በጥፊ ቀይዋን በከዘራ» የሚሉት ይገኙበታል።
በተለያዩ አጋጣሚዎችና ክስተቶች የተሰየሙ፣ በሀገሪቱ በሚገኙ ብሔረሰቦች ስም የተሰዬሙ፣ በጣልያን ወረራ ዘመን ስያሜ ያገኙ ሰፈሮችም አሉ፡፡ አዲስ አበባ በቦሌ ውበትና ዘመናዊነት፣ በመርካቶ ድምቀት፣ በጨርቆስ ፍጥነት፣ በአራት ኪሎ ታሪካዊነት ደምቃ በአራዳ ልጆች አርዳ፣ በፒያሳ፣ በካሳንችስ፣ በጦር ኃይሎች፣ መገናኛ፣ ሀያት እና ሌሎች ለመጥራት በሚታክቱ ስሞች በዝታ ኢትዮጵያውያንን ፣ አፍሪካውያንን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብን ሰብሳባ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
እንደ መታደል ሆነና አዲስ አበባ የደረስኩት በምሽት ነበር፡፡ በመብራት አሸብርቃ ስትታይ እሳት የታያያዛት ይመስላል፤ አቤት ጉድ! ስል ተገረምኩ፡፡ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የነበረው ሰው አብዛኛው በውበቷ እንደተማረከ ቢያሳብቅም እንደኔ የተገረመ ግን ያለ አልመሰለኝም፡፡ ከአጠገቤ በተከፈተችው የመኪናው መስታውት ዓይኖቼን አሾልኬ በሚታዬኝ ልክ ከላይ ወደታች ተመለከትኳት፡፡ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚመስል መልኩ የተሰሩት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ከግርጌያቸው ያለችውን ትንሽ ቤት ከማዬት ይልቅ ሰማይን አንጋጠው ይመለከታሉ፡፡ የዘመኑ ሰው ብቻ ሳይሆን የዘመኑ ሕንጻዎችም የግርጌያቸውን አለማዬታቸው ገረመኝ፡፡ የሚያበሩት መብራት ወደ ሰማይ ተወንጭፎ በአዲስ አበባ ሰማይስ ስር የሚገኘውን ደመና የጋዬ አስመስሎታል፡፡ መኪናችን ቁልቁለቱን ሲወርድ ዓይኔም ከሰማይ ጠቀሱ ፎቅ ወደስር ወዳሉት ቤቶች ተመዘግዝጎ ወረደ፡፡ ለደመናው ጭምር የሚያበሩ ቤቶች እንዳሉ ሁሉ አቅም ያነሳቸው መብራቶች እንዳሉም ተመለከትኩ፡፡
ከተማዋ ውስጥ ገብተናል፤ ከእንጦጦ ተራራ ላይ ሆኜ ከተመለከቱኩት የከተማ መብራት ድምቀት የበለጠ በከተማዋ ውስጥ የሰውና የመኪና ድምጹ ጫጫታ ይደምቃል፡፡ የመኪናው ማንቂያ ድምጽ፣ የተለያዩ ቦታዎችን እየጠሩ ተጓዥ የሚጠይቁ የታክሲ ረዳቶች፣ ምግብና አልባሳት ለመሸጥ እያዞሩ የሚጮሁ ገበያተኞች፣ በየመጠጥ ቤቶች ተቀምጠው እየተጠጡ በነጻነት የሚንጫጩ ጠጪዎችና የተለያዩ ደምጾች ሲስተጋቡ ከተማዋን አጋሏት፡፡
የእትጌ ጣይቱን አዲስ አበባንና የዛሬቱን አዲስ አበባ አገናኚቼ ለማሰብ ሞከርኩ፤ የማይቻል ነው፡፡ ለውጣቸው ስለገዘፈብኝ ተገርሜ ተውኩት፡፡ መኪናችን መርካቶ አውቶብስ ተራ አድርሶን የነበረበትን ግዴታ እንደጨረሰ በረዳቱ አመካኝነት ተነገረን፡፡ እኛም በሠላም ያደረሱንን ፈጣሪና ሾፌር እንደየእምነታችን እያመሠገንን ወርደን በተለያዬ አቅጣጫ ተበተን፡፡
በአዲስ አበባ ድህነት የማያውቁ ዝነኛ ሀብታሞች፣ ሀብት ምን እንደሆነ የማያውቁ መናጢ ደሀዎች፤ ሳይኖራቸው የሚያጎርሱና የሚያለብሱ ደጎች፤ ከዓይን በፈጠነ ቅልትፍና ባዶ የሚያስቀሩ ጥቂት ሌቦች፤ አጀብ በሚያሰኝ አልጋ የሚተኙ የሀብታም ልጆች፣ ማደሪያ አጥተው በውኃ መውረጃ ቱቦ ስር የሚተኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሌሎችም የሕይዎት ተቃራኒ የሆኑ ጉዳዮች ይገኙባታል፡፡
ወደቤት ሲገባ ጫማ ተጽድቶ የሚገባባቸው ቤቶች፣ በየሰዓቱ የሚጸዱ ጎዳናዎች፣ የቆሻሻ መደርደሪያ የሚመስሉ መንገዶችም ይገኛሉ፡፡ አዲስ አበባ በቆዳ ቀለም፣ በዘርና በሃይማኖት የማይመሳሰሉ ሰው በመሆናቸው ግን ተመሳስለው የሚኖሩባት ከተማም ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ‹ማጥ ውስጥ ናቸው› ብሎ የሚጨነቅ ፍጡር ካለ አዲስ አበባ መሄድ መፍትሔው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዴት በፍቅር እንደሚኖሩ አብሮነትንና ሕብርን ከዚያ ሲያይ ማጥ ውስጥ አለመሆንን ያያል፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን አስጊ ደረጃ ላይ ሳይሆን አጓጊ ደረጃ እንዳሉ ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃናም ይሁን የተጣመመ በፍቅር የቀናውን በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ኢትዮጵያዊነት የማፍረስ አቅም የለውም፡፡ ላፍርስ ቢል እንኳን አፍርሰው እንደሚሠሩት ፍቅራቸውና አንድነታቸው ምስክር ነው፡፡ አዲስ አበቤዎችና ኢትዮጵያውያን የሚፈርሱ ቢሆን ጣልያን ያፈርሳቸው ነበር፤ ይልቅኑስ የችግር ቀን ፍቅር ሰጥቷቸው ዘመናቸውን ዘላለማዊ አደረገው፡፡
በምሽት መብራቶች ስር ሆኜ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በዝግታ እየተጓዝኩ ለሽርሽር ዱባይ፣ ሞሮኮና ሌሎች የዓለም ሀገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ዝነኞችንና በየመንገዱ ተኝተው የተረፈ ምግብ የሚለምኑት ድሆችን በአንድ ከተማ መኖር ሳይ አብዝቼ ተገርምኩ፡፡ ሌላ ሐሳብም መጣብኝ ‹ዩኔስኮ› ፍቅርና አንድነትን ለምን አልመዘገበም? ስል ለራሴ ጠየኩ፡፡ ዩኔስኮ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር በዓል ከሚመዘግብ ከዓመት እስከ ዓመት የማይጠፋና የሚከበር ሳይሆን የሚኖር ፍቅር እና አንድነትን ቢመዘግብ ይሻለው ነበር ስልም አሰብኩ፡፡ ምን አልባትም ወደፊት የፍቅር ከተማ ብሎ ይመዘግባት ይሆናል፡፡
በዓድዋው ጦርነት ጊዜ በርካታ ገድሎችን እንደፈጸመና አብሮ እንደዘመተ የሚነገርለት የአራዳው ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ምልክት ነው፡፡ በስሙም ሰፈር ተሰይሞለታል፡፡ አራዳ ከጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕክል እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በርካታ ማኅበራዊ ክዋኔዎችም ይከወኑበት የነበረ በመሆኑ የዚያ ዘመን አዝማሪዎች እንዲህ ሲሉ አዚመውለታል፡፡
«ሱሪ ያለቀበት አይገዛም አዲስ፣
ወይ አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ።
እስኪ አራዳ ልውጣ ብርቱካን ባገኝ፣
ትናንት ኮሶ ጠጣሁ ዛሬ መረረኝ።
ምነው በአደረገኝ ከአራዳ ልጅ መሣ፣
እንኳን ለገንዘቡ ለነፍሱ የማይሣሣ።
የአራዳ ዘበኛ ክብሬ ነው ሞገሴ፣
በቸገረኝ ጊዜ የሚደርስ ለነፍሴ» እያሉ፡፡
አዲስ አበባ ለቁጥር የሚታክቱ የተለያዩ ቤተ እመነቶች ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የደነቀኝ ከአንድ የኮንዶምንዬም ሕንጻ ውስጥ የተለያየ ብሔር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ያላቸው ዜጎችን በማዬቴ ነው፡፡ ፍቅር በአንድ ሕንጻ ውስጥ እስከ ወዲያኛው ያኖራል፡፡ ልዩነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም አንድነትን ደግሞ መኖሪያ ዘዴ አድርገውታል፡፡ ታዲያ ልዩነትን የውበት ሸማ አድረገው በአንድ ድንኳን ስር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ማን ይለያቸዋል? ስል ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡
አዲስ አበባ በቆዬሁባቸው ጊዜያት ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ደስታንና ተስፋን አየሁ፡፡ በተለይም በቀን የመኪናውና የሰው ትርምስ አጀብ ያሰኛል፡፡ ከተማዋን እየከፈለ የሚንጎራደደው ባቡርም ሌላኛው ውበትና ሀብት ነው፡፡ በመልካሟ ምድር ብዙ መልካም ነገር አየሁ፡፡ አሁን አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን አዲስ ተስፋም ናት፡፡ በቆይታዬ ረክቻለሁ፡፡ መልካም ነገርም ሸምቻለሁ፡፡ እቃ ሳይሆን ምግባር፣ ወሬ ሳይሆን ተግባር ገዝቻለሁ፡፡ እርስወስ ምን ይገዙባት ይሆን ሠላም እና ፍቅር ተመኘሁላት፡፡ ሠላም ለኢትዮጵያ!
በታርቆ ክንዴ