በሰሜን ሽዋ ዞን ስድስት ወረዳዎች ሁሉን አውዳሚ ተምች መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

90

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ 7 ሺህ 537 ሄክታር መሬት ላይ በተደረገ አሰሳ 5 ሺህ 60 ሄክታር የእርሻ እና 307 ሄክታር የግጦሽ መሬት በሁሉን አውዳሚ ተምች መወረሩ ተረጋግጧል፡፡ 25 ቀበሌዎችን ማዳረሱም ታውቋል።
ከመምሪያው በተገኘው መረጃ መሠረት በተለይ የአፍሪካ ተምች በሦስት ወረዳዎች ላይ በወረርሽኝ ደረጃ ነው የተከሰተው።

በሌላ በኩል በወረርሽኝ ደረጃ የተከሰተባቸውን ጨምሮ በስድስት ወረዳዎችም የአሜሪካ መጤ ተምች በመደበኛ ደረጃ መከሰቱን መምሪያው አረጋግጧል።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ተውልኝ ሽባባው እንዳሉት በ 3 ሺህ 353 ሄክታር ላይ የመከላከል ሥራ ተከናውኗል። ለዚህም 3 ሺህ 676 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል።

መምሪያው በዋናነት ሁሉን አውዳሚ ተምች በወረርሽኝ ደረጃ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ትኩረት ማድረጉን ያነሱት አቶ ተውልኝ ክስተቱ በመደበኛ ደረጃ በታየባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ እንዲከላከል የማድረግ ሥራ መከናወኑን አመላክተዋል፤ የእለት ከእለት ቅኝት ማድረግና ክስተቱ ከታዬም አስቸኳይ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ወቅቱ የአገዳ እህል የበቀለበት ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገዳ ቆርቁር አና ቆራጭ ትልን ጨምሮ ለጸረ-ሰብል ተምች ክስተት ምቹ ወቅት በመኾኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ አንደሚሻ ነው አቶ ተውልኝ ያስገነዘቡት።

ተምች በባሕሪው በፍጥነት ሁሉን አውዳሚ በመኾኑ በምርት ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ይጠይቃል፤ ለዚህም የግብርና ባለሙያዎች፣ የአሥተዳደር አካላትና አርሶ አደሮች በልዩ ትኩረት ሊከታተሉት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የተምች ክስተቱ ከሚያዚያ 25/2015 ዓ.ም ጀምሮ የታዬ ሲኾን አሁን ላይ በፍጥነት አድማሱን ያሰፋ ስለመኾኑ ተመላክቷል።

በዞኑ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የሁሉን አውዳሚ ተምች ክስተት የተለመደ መኾኑንም አቶ ተውልኝ አንስተዋል፤ የመከላከል ሥራውም ሁሉን አካታች በኾነ መልኩ መጠናከር አለበትም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከግህንብ እስከ እመን አላምንም!”
Next articleበአማራ ክልል የሚገኙ የማዕድን ሃብቶችን በስፋት በማጥናት ዘርፉን ሁነኛ የሃብት ምንጭ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።