
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም በርካታ ጦርነቶችን አስተናግዳለች ይባላል፡፡ የሚመራውን ሕዝብ በዘር ለይቶ ያጠቃ ሥርዓትም ሆነ መንግሥት ግን ከኢትዮጵያ ውጭ አልታየም ብለው የሚሞግቱት በርካቶች ናቸው፡፡ በዘመነ ቅኝ ግዛት ምዕራባዊያን ወራሪዎች ድንበር ተሻግረው ንጹሃንን ጨፍጭፈዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ታንዛኒያ፤ ከአንጎላ እስከ ሩዋንዳ፤ ከላይቬሪያ እስከ ሴራሊዮን ዘርን መሰረት ያደረጉ የዘር ማጽዳት ወንጀሎች በዓለም ላይ ታይተው አልፈዋል፡፡ ነገር ግን በተራዘመ እና ሀገር በቀል ሥርዓታዊ ድጋፍ የተዘጋጀለት መዋቅራዊ ጭፍጨፋ ከኢትዮጵያ ውጭ ተፈልጎ ብዙም አይገኝም ነው የሚባለው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ፤ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት ባምላክ ይደግ (ዶ.ር) በወልቃይ ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች ላይ ለሦስት አስርት ዓመታት የተፈጸመው የዘር ማጽዳት ዘመቻ አቻ የሌለው ነው ይላሉ፡፡ ዶክተር ባምላክ ይደግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች ላይ በተፈጸመው መዋቅራዊ የዘር ማጽዳት ወንጀል ዙሪያ ባሰማራው የጥናት ቡድን ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ጥናት ዘርፍ ቡድን አስተባባሪ ናቸው፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች የህወሃት አገዛዝ ዘመን የተራዘመ ጭፍጨፋ መንግስታዊ እርካብን ሳይቆናጠጡ ይጀምራል የሚሉት ዶክተር ባምላክ የዘር ማጽዳት ዘመቻው በወቅቱ የነበሩት ታጣቂ ሽፍቶች እግራቸው ተከዜ ወዲህ ማዶን ከተሻገበረት ወርሃ ነሐሴ 1972 ዓ.ም ይጀምራል ነው የሚሉት፡፡
በወቅቱ በጎንደር ክፍለ ሀገር ሥር የትዳደሩ የነበሩት እነዚህ አማሮች ተከዜን ተሻግረው የሚመጡ ሽፍቶች የሚፈጽሙትን አፈና፣ ዝርፊያ፣ ግድያ እና ስርቆት እንደ ተራ ወንጀል በመቁጠር ጥቃቱን ከመከላከል እና ከመመከት ያለፈ የኅይል እርምጃ አይወስዱም ነበር፡፡
በወቅቱ የነበሩ የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳደራዊ መሪዎችም ለአውራጃ መሪዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጠቅሰው እና ችግሩ የተፈታበትን መንገድ አብራርተው ከመግለጽ ውጭ የተራዘመ ሥጋት እና ጥርጣሬ ስላልነበራቸው ችግሩን ጉዳይ ብለው አያራግቡትም ነበር፡፡ እየቆየ ሲመጣ ግን ችግሩ በመደጋገሙ እና ለአካባቢው ሠላም ሥጋት በመሆኑ የተጻጻፏቸው መረጃዎች በሰነድነት በግለሰቦች እጅ ይገኛል፡፡
ህወሐት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች ላይ የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል በምክንያቱ አቻ የለውም የምንለውም ከዚህ ላይ ነው የሚሉት ዶክተር ባምላክ ከእርስታቸው ድረስ መጥቶ፣ ከመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን ንጹሃን እና አካባቢያችሁን መልቀቅ አለባችሁ ተብሎ የተጨፈጨፈ የዓለም ሕዝብ ያለ አይመስለኝም ነው ያሉት፡፡
የህወሃቶች ወረራ እና በአካባቢው ላይ ያላቸው ትኩረት ግልጽ እየሆነ የመጣ ግን በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት ወደ ሱዳን የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆችን ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ወቅት ነበር ይላሉ ዶክተር ባምላክ፡፡ ህወሐቶች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ድንበር በመፍጠራቸው ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተጭበረበረ መረጃ ለማድረስ እድል እንደተፈጠረላቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የአካባቢውን ዲሞግራፊ ሙሉ በሙሉ ለመቀየር በአማራዎች ላይ ከሚፈጽሙት የዘር ማጽዳት ዘመቻ በተጨማሪ ከመሃል ትግራይ ነዋሪዎችን በማምጣት ማስፈር ጀምረው ነበር፡፡
የ1977 ዓ.ም ድርቅን ተከትሎ በተከሰተው ርሃብ ከመሃል ትግራይ ተነስተው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዓለም አቀፋዊ ጥረት ይደረግ ነበር የሚሉት የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ ተፈናቃዮቹ የመመለሻ ቅጽ ሲሞሉ ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ፍላጎት ነበራቸው ይላሉ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበሩት የህወሃት ታጋዮች ሽሬ፣ አድዋ፣ ተንቤን ሄዳችሁ ምን ልትበሉ ነው በማለት አስገድደው ከወልቃይት እስከ ራሁያን፣ ከማይካድራ እስከ በረከት፣ ከሁመራ እስከ ቃፍቲያ ተፈናቃዮችን ለማስፈር አስገድደው ቅጽ ያስሞሏቸው እና እያመጡ ያሰፍሯቸው ነበር፡፡
የትግራይ ተወላጆችን በወረራ በያዟቸው አካባቢዎች የማስፈሩ ሂደት የተራዘመ እና ያልተቋረጠ ነበር የሚሉት ዶክተር ባምላክ 1991 ዓ.ም በነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳይቀር የትግራይ ሕዝብ ጓዙን ጠቅልሎ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አካባቢዎች በመደበኛ ሁኔታ ያስፈሩ ነበር ነው ያሉት፡፡
በወቅቱ ስለነበረው ያልተቋረጠ ሰፈራ በርካታ መረጃዎች እንዳሉ የሚያነሱት የጥናት ቡድኑ አስተባባሪው 1986 ዓ.ም ኢራቅን ለመውጋት ከመጣው የአሜሪካ ወታደር ሬሽን (ስንቅ) የተረፈው በአማራ ምድር ለሰፈሩት የትግራይ ተፈናቃዮች “ከአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት የተሰጠ” ተብሎ ተጽፎበት ይታደል ነበር ነው የሚሉት፡፡
ባልተቋረጠ ሂደት ከሚደረገው ሰፈራ ጎን ለጎን “አማራ ነን” ባሉ የአካባቢው ተወላጆች ላይ እስርን ጨምሮ መሰወር፣ እንዳይናገሩ መርፌ መውጋት፣ ግድያ፣ ማስቃየት እና መሰል የዘር ማጽዳት ዘመቻዎችን ይፈጽሙ ነበር፡፡
በአካባቢው ከ10 በላይ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል የሚሉት ዶክተር ባምላክ በርካታ ታሪክ አዋቂ እና ሞጋች አማራዎች አስከፊ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል ነው የሚሉት፡፡ ህወሃቶች በአካባቢው ለሚፈጽሙት ወንጀል በቂ ምክንያት ባይኖራቸውም ከግህንብ እስከ እመን አላምንም በተባሉ አካባቢዎች አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ነው የሚሉት፡፡
ግህንብ በትግሪኛ ገሃነብ እንደማለት ሲሆን በአካባቢው ከሚፈጸመው ወንጀል ጋር ተያይዞ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ስያሜ እንደተሰጠው ይናገራሉ፡፡ እመን አላምንም ቦታው ገደል በመሆኑ እመን ተብሎ ያላመነ አማራ ወደ ገደሉ ሲወረወር ያመኑት ደግሞ ወደ ሌሎች ማሰቃያዎች ከማዛዎራቸው ጋር ተያይዞ “እመን አላምንም” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው በጥናቱ ያካተትናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ ብለውናል ዶክተር ባምላክ፡፡
ህወሃት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች ላይ ከፈጸሙት የዘር ማጽዳት ዘመቻዎች ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ሊማረው የሚገባ እውነት አለ የሚሉት ዶክተር ባምላክ ተሰውሮ የሚቀር፣ ቀን ጠብቆ የማይገለጥ እና የማይገለበጥ ሃቅ የለም፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት እና ራያ አማራዎችን ጭፍጨፋ ዓለም በተለይም ደግሞ የቀንዱ ፖለቲካ ዘዋሪ ሀገራት ያውቁ ነበር ብቻ ሳይሆን መስቆምም ይችሉ ነበር ያሉት ዶክተር ባምላክ ዝምታቸው በአካባቢው ላይ የራሳቸው የሚሉትን ሥርዓት ለማንበር ከመሻታቸው የመነጨ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ቀደመ ማንነታቸው የተመለሱ አካባቢዎችን መንግሥት ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባ ነበር የሚሉት ዶክተር ባምላክ የሚስተዋለው ግን ተቃራኒውን ነው ብለዋል፡፡
በጀት አለመመደብ፣ ሥነ-ልቦናቸውን አለማከም፣ አለመካስ እና እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፈጽሞ አለማየት ሌላ ጥቃት ተደርጎ የማይታይበት ምክንያት የለም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!