የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ክብራቸውን የሚመጥን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን የልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤቱ ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ገለፁ፡፡

46

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓመለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤት በ2015 የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ 47 ተማሪዎችን ሀገር አቀፍ ፈተና ያስፈትናል፡፡

የሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ8ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እያስተማረ ይገኛል።

ልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤቱ በ2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ 47 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ሲያስፈትን ተማሪዎቹም አርበኛ፣ ፖለከቲከኛና ጸሐፊ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ክብራቸውን የሚመጥን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ከትምህርት ቤቱ መምህራን መካከል ባይለየኝ ኪዳን ተማሪዎቹን ለተሻለ ውጤት እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ብቃት፣ስነምግባርና የጊዜ አጠቃቀም ለእኛ መምህራን ትልቅ ብርታት ሰጥቶናልም ብሏል መምህር ባይለየኝ።

የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፈለኝ ተማሪዎቹን በሀምሌ ወር ለሚሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና በየትምህርት መስኩ፣ በስነ-ምግባርና በስነ-ልቦና ዝግጁ አድርገናል ያሉ ሲሆን ከተማሪዎቹ ከፍተኛ ውጤት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡

የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤት የዚህ ዓመት ተፈታኞችን ጨምሮ በአማራ ክልል ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 150 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፦ዘላለም አስፋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምባሳደር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ከሚገኙ ከ36 በላይ የዳያስፖራ አደረጃጀት ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ተወያዩ።
Next article“ከግህንብ እስከ እመን አላምንም!”