
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አምባሳደር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ከሚገኙ ከ36 በላይ የዳያስፖራ አደረጃጀት ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱም በአገራችን ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች፣ የገጠሙ ፈተናዎችና መፍትሄዎቻቸው፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነበር። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዙሪያ ከቤተ-እምነቶች እና መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የዳያስፖራው ተሳትፎ፣ በሁለትዮሽ ግንኙነትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይም መወያየታቸው ተገልጿል።
በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መንግስት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተወሰዱት እርምጃዎችን አምባሳደር ስለሺ በውይይቱ ላይ ለአብነት አንስተዋል። ከእምነት ተቋማትና ከመኖሪያ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ለኤምባሲው በአካልና በተለያዩ መንገዶች መቅረባቸውን ጠቁመው ህግን በማስከበር ሂደት ካለፉት ክፍተቶች በመማር መንግስት ህዝቡን ያማከሉ አካሄዶችን እንደሚያስቀድም ጠቅሰዋል። ሀገሪቷ ባለፉት ጥቂት አመታት ከውስጥም ከውጭም በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ዳያስፖራው ላበረከተው ሁሉን አቀፍ ገንቢ አስተዋጽኦም አመስግነዋል።
ወቅቱ ሀገራችን ከነበሩባት ፈተናዎች ወጥታ ወደምትታወቅበት ሰላምና ፈጣን ልማት እንድትገባ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለትውልድ የሚሻገር አሻራ ለማሳረፍ ሁለም መረባረብ እንዳለበት አምባሳደር ስለሺ አስረድተዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአረብ ሊግ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መግለጫዎችና አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ሳታስደፍር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ከተመሰረተው አቋሟ ዝንፍ እንደማትልም ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም መንግስት ህግን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ንጹሃንን ለእንግልት የማያጋልጡ እንዲሆኑ፣ ለውይይት ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ የወሰዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የመረጃ ፍሰት እንዲጎለብትና ሌሎች ሃሳቦች ያነሱ ሲሆን የሚያደርጉትን ድጋፍም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!