“በበቂ መጠን እና ዓይነት ምርጥ ዘር ቀርቧል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

92

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለሚዘሩ ሰብሎች በበቂ መጠን እና ዓይነት ምርጥ ዘር መቅረቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል። አርሶአደር ጌትነት ባስሌ በሰሜን አቸፈር ወረዳ የይስማላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ማሳቸውን በምርጥ ዘር ለመሸፈን ጥረት እያደረጉ መኾኑን ነግረውናል፡፡

አርሶአደር ገበያው እስከዚያ የሰሜን አቸፈር ወረዳ አምበሽንጀሀር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ መንግሥት ባቀረበላቸው የበቆሎ ምርጥ ዘር ማሳቸውን ሸፍነዋል። ቀሪውን ማሳ በሌሎች ሰብሎች ለመሸፈን ማሳቸውን እያዘጋጁ ነው። መንግሥት የሌሎች ሰብሎችን ምርጥ ዘር በወቅቱ እና በዓይነት እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል።

የሰሜን አቸፈር ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ንጉሥ አለነ በወረዳው 800 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር መቅረቡን ተናግረዋል። የቀረበውን በፍትሐዊነት ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። የሌሎች ሰብሎችን ምርጥ ዘር አስቀድመው ለማምጣት እና ለማሰራጨት ከሚመለከተው አካል ጋር እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምሥጋናው ወልደልዑል “ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘርን እንደየሚዘሩበት ወቅት የሚቀርብበትን መንገድ እያመቻቸን ነው” ብለዋል፡፡
እንደ ምዕራብ ጎጃም ዞን ከ44 ሺህ 240 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቧል፣ 38 ሺህ 741 ኩንታልም ተሠራጭቷል ነው ያሉት። አቶ ምሥጋናው አርሶ አደሩ ከዘልማድ አሠራር ወጥቶ በግብርና ምክረ ሃሳብ መሠረት የቀረበለትን ዘር በአግባቡ እንዲጠቀምም መክረዋል፡፡

የአማራ ክልል የግብርና ግብዓቶችና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ እንዳሉት በክልሉ 94 ሺህ 652 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ቀርቧል፡፡ ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 81 ሺህ 827 ኩንታል መሠራጨቱን አንስተዋል። ቀሪ ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ከበቆሎ በተጨማሪ የሚዘሩ ሌሎች ሰብሎች የማሣ ስፋትን እና ፍላጎትን መሠረት ተደርጎ በቀበሌ ተደልድሎ መውረዱንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የማኅበረሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ አድጓል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
Next articleአየር መንገዱ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘ።