“በአንድ እጅ ነጻነት፣ በሌላው እጅ ልማት – ወልቃይት”

292

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እነዚያ ብርቱ ክንዶች ሳይዝሉ ኖረዋል፣ እነዚያ ጀግኖች ከልባቸው ላይ እንደታጠቁ ዘመናትን ተሻግረዋል፣ እነዚያ ልበ ሙሉዎች የመከራውን ዳገት አልፈዋል፣ እነዚያ የበረሃ መብረቆች፣ አይደፈሬ አንበሶች ለእውነት ኖረዋል፣ በእውነት ታግለዋል፣ ስለ እውነት ጸንተዋል፡፡ የጨለማውን ዘመን በጽናት እና በጀግንነት አልፈዋል፣ የሰቆቃውን ማዕበል በብርታት ተሻግረዋል፣ ጣልናቸው ያላቸውን ጠላት ጥለውታል።

የራሳቸውን አይሰጡም፣ የሌላውን አይጠይቁም፣ በግፍ አይዘምቱም፣ የሰው አይወስዱም፣ ለክብር ይሞታሉ፣ ለታሪክ ለመስዋዕት ይዘጋጃሉ፣ ለነጻነት የሞት ጽዋን ይጎነጫሉ፡፡ በአባታቸው ባድማ በኩራትና በክብር ይኖራሉ፣ በጀግንነት እና በልበ ሙሉነት ይመላለሳሉ፡፡ ከአባት ባድማ የሚገፋቸው፣ ተወልደው ካደጉበት፣ ታሪክና ሃይማኖት፣ የጸና ቃል ኪዳን ከተቀበሉበት ሥፍራ የሚነካካቸው በመጣ ጊዜ ይቆጣሉ፡፡ ቁጣቸው አይበርድም፣ ክንዳቸው አይቻልም፣ ያደቅቃል፣ እንዳልነበሩ ያደርጋል እንጂ፡፡

ዘመን ያመጣቸው ገፍተው፣መከራ አብዝተው፣ የአባት የእናት፣ የአያት ቅድመ አያት ሥፍራ ነጥቀው፣ ሊያኖሯቸው ተፍጨረጨሩ፡፡ እነርሱ ግን የአባትን ማጣት፣ ነጻነትን መቀማት በታሪካቸው አያውቁምና አምርረው ታገሏቸው፣ በጽናት ተዋጓቸው፣ በጀግንነት ድል መቷቸው፡፡ መከራ ስናበዛባቸው፣ ሞትና መሳደድ ሲበረክትባቸው ይተውታል፣ የአባትና የእናታቸውን ባድማ ይረሱታል ብለው አስበው ነበር፡፡ ዳሩ ጀግኖችን አብዝተው አሰባሰቧቸው፣ አጠነከሯቸው፣ እንደ አለት አጠነከሯቸው እንጂ አልተሳካላቸውም፡፡ ጀግና በመከራ ይጠነክራል እንጂ በመከራ አይዝልምና፡፡

ጀግንነትን በደም የወረሱት፣ አስተዋይነትን፣ አርቆ አሳቢነትን እና ትዕግሥትን የታደሉት የወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሑመራ ጀግኖች የገፋቸውን ጥለው፣ የነካቸውን አሽቀንጥረው ተወልደው ባደጉበት፣ ታሪክና ቃል ኪዳን በተቀበሉበት ሥፍራ ልማት ላይ ናቸው፡፡

ከዓመታት የጸና ተጋድሎ፣ ለእውነት ከተከፈለ መስዋዕትነት በኋላ ነጻነታቸውን እያጣጣሙ፣ ሰላማቸውን እየጠበቁ፣ በመልካም ማሳ እያረሱ፣ በሰፊ አውድማ እያፈሱ መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በቀኝ በግራ ሲነሳባቸው የነበረውን ትንኮሳ እየመከቱ በልማታቸው ቀጥለዋል፡፡ በጠንካራ ክንዳቸው ለትንኮሳዎች የጀግና መልስ እየሰጡ ልማት ላይ ናቸው፡፡ ዘንድሮም ከቀድሞ በበለጠ ለማልማት ዝግጅት ላይ መኾናቸውን ነግረውኛል፡፡

በአንድ እጃችን ነጻነታችንን እንጠብቃለን፣ በሌላኛው እጃችን ልማታችንን እናስቀጥላለን ነው ያሉኝ፡፡ በልማት የተሰማሩት ርስቀይ አደመ የክረምቱን መግባት ተከትሎ በወልቃይት ጠገዴ ጥሩ የልማት ጅማሮ መኖሩን ነግረውኛል፡፡ ዘንድሮ ከወትሮው በተሻለ መልኩ ለማልማት ወደ ልማት ዞረናልም ነው ያሉት፡፡ ከልማት ጎን ለጎን የተናበበ የሰላምና የፀጥታ ጥበቃ እያደረጉ መኾናቸውንም ነግረውኛል፡፡

የማይካድራ አማራዎችን ጨፍጭፎ የሄደው የሳምሪ ቡድን አሁንም ትንኮሳ እንደሚያደርግ የተናገሩት ርስቀይ ዓላማው ልማት ለማደናቀፍ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ወደ ሱዳን ጠረፍ በሚገኙ የልማት አካባቢዎች ላይ በሠራተኞች ላይ ትንኮሳ እንደሚፈጥርም ነግረውኛል፡፡ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በቅንጅት አካባቢያቸውን እንደሚጠብቁ የተናገሩት ርስቀይ ምንም ሊያመጣ እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይሄን ገዳይ ቡድን ሊያስታግሰው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ኢንቨስተሮች መሬታቸውን ለሰብል በሚያጸዱበት ወቅት የሳምሪ ቡድን ወደ ሠራተኞች እንደሚተኩስም ተናግረዋል፡፡

በፍጹም ሰላም ባለሀብቶች ወደ ልማት እንዲቀጥሉ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ሊያስታግሳቸው ይገባልም ብለዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ ነጻነቱን፣ ሰላሙን እና ማንነቱን እያጣጠመ ነው፣ ነገር ግን ሰላሙና ነጻነቱን የበለጠ እንዲያጣጥም መንግሥት የወልቃይት ጠገዴን ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ወልቃይት ጠገዴ የእውነት ጥያቄ ነው የጠየቀው፤ የማንንም አይፈልግም፣ የሌለውን ስጡኝ አይልም፣ ማንነቱ እና በታሪክ፣ በመረጃና በማስረጃ የተደገፈው እውነቱ ግን ሊከበር ይገባል ነው ያሉት፡፡

በማንም ላይ ጥላቻ የለብንም፣ የራሳችንን ግን ለማንም አንሰጥም፣ አማራዎች ነን ማንነታችን ሊከበር ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡ የወልቃይት ጥያቄ እንደሚመለስ በትዕግስት እየጠበቅን ነው፣ የወልቃይትን የእውነት ጥያቄ በአስቸኳይ መመለስ ለሀገር፣ ለሕዝብና ለመንግሥት ጠቃሚ ነውም ብለዋል፡፡ ወልቃይት ላይ ትንኮሳ ለማድረግ የሚፈልጉት ኀይሎች አሁንም ሙሉ ለሙሉ አላቆሙም ነው ያሉት፡፡

“ሁልጊዜ ሞኝነት የለም፣ በተጠንቀቅ ላይ ነው ያለነው” ያሉኝ ርስቀይ በአንድ ወገን ለልማት በሌላ ወገን ደግሞ ለደኅንነት እና ለነጻነት እንቆማለን ነው ያሉኝ፡ ሙሉ ለሙሉ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ መንግሥት ተንኳሾችን አደብ ሊያስገዛቸው፣ እረፉ ሊላቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

ሌላኛው በእርሻ ልማት የተሰማሩት ሀብቱ ተሻለ በወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች እና ባለሀብቶች ግፍ ይሠራባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከብርቱ ትግል በኋላ ከተገኘው ነጻነት ወዲህ ግን ያለከልካይ በቀያቸው እያለሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከልማታቸው ጎን ለጎን ሰላማቸውን እየጠበቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሰላሙን ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት መጠበቅ ግዴታችን ነውም ብለዋል፡፡

ወልቃይት ላይ ትንኮሳ ለማድረግ የሚሞክር ካለ አይሳካለትም፤ ከልማታችን ጎን ለጎን ሰላማችንንም እናስከብራለን ነው ያሉት፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ከሰው አይደርስም፣ በሰላሙና በነጻነቱ ላይ ከመጡበትም አይታገሰም፣ በጠንካራ የሥነ ልቦና ዝግጅት አካባቢውን ይጠብቃልም ብለዋል፡፡ ጠላቶች ወልቃይት ላይ ለመተንኮስ ያስባሉ፣ ነገር ግን አይሳካላቸውም፣ በነጻነቱ እና በማንነቱ ለሚመጣበት የትኛውም አካል ከባድ መልስ ይሰጣል፣ ማንንም አይታገስም ነው ያሉት፡፡

ልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ሳይነጣጠሉ የሚቀጥሉ ጉዳዮች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ የትኛውም ችግር የማይበግረው እና ከዓላማው የማይናወጥ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ልማት በሁሉም ዘርፍ የተሻለ እንዲኾን በጀት ሊለቀቅለት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በቅንጅት አካባቢውን እየጠበቀ ልማቱንም እያለማ ነው ብለዋል፡፡ አሉባልታዎችን ወደ ጎን እየተወ እውነታው ላይ እንደሚያተኩርም ገልጸዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ለምለሙ ባየህ አሁን ላይ ሁሉም ወደ ሥራ ገብቶ ልማት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢውን ሰላም የማይፈልጉ በተለያየ አቅጣጫ ፕሮፖጋንዳዎችን ይነዛሉ፣ ነገር ግን ለጠላት ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ሳይሰጥ ልማቱን እያለማ ነውም ብለዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩም በጥምር አስተማማኝ የኾነ ጥበቃ እያደረገ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

ማይካድራ ላይ የዘር ጭፍጨፋ አድርጎ የሸሸው ቡድን ከትንኮሳ እንደማያርፍ የተናገሩት ምክትል መምሪያ ኀላፊው ልማትን ለማደናቀፍ ሙከራ ያደርጋል፣ አልተሳካለትም፣ ወደፊትም አይሳከለትም ነው ያሉት፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ ሊሰነዘር የሚችልን ትንኮሳ ታሳቢ ያደረገ አስተማማኝ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፤ሁልጊዜም ቢኾን ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ ልማቱ በተፈለገው ልክ እንዲሳካ ዝግጅት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ አጠራጣሪ ነገሮች ሲታዩ ለፀጥታ መዋቅሩ እንዲያሳውቅም አሳስበዋል፡፡ ባለሀብቶች ያለምንም ስጋት አካባቢያቸውን እንደሚያለሙም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኮሚቴው የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በቅንጅት መሠራት እንዳለበት አሳሰበ።
Next article“የማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ የማኅበረሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ምጣኔ አድጓል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ