
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ቋሚ ኮሚቴው የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክትን ተዘዋውሮ ተመልቶ የጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ የሥራ ተቋራጭ ድርጅቱና የአማካሪ ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የማጠቃላያ ግብረ-መልስ ሰጥቷል፡፡
የቡድኑ አስተባባሪ መዓዛ ጥጋቤ የግድብ ሥራ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ተቋራጭ ድርጅቱና የአማካሪ ድርጅቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ የሲሚንቶ፣ ብረት፣ ነዳጅና ሌሎችም ግብዓቶች አለመሟላት ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ሠራተኞችንና የሠራተኛ ማኅበር ተወካዮችን ባነጋገሩበት ወቅት እንደ ችግር መነሳቱን ጠቁመው፤ ችግሮቹ እንዲፈቱ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የውኃ መሠረተ-ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በእምነት ጋሻው በበኩላቸው ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀትና በመሥራት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለቡድኑ አባላት አስረድተዋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችም በበኩላቸው፤ የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያያደርጉ መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!