የክረምት ወቅትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን የወባ በሽታ ለመከላከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አሳሰበ።

50

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መምሪያው ለአሚኮ በሰጠው መረጃ የክረምቱን ወቅት ተከትሎ የወባ በሽታ ሥርጭት መጨመሩን ገልጿል። የባሕር ዳር ከተማ ጤና መመሪያ ኀላፊ አስማማው ሞገስ እንደተናገሩት በከተማዋና አካባቢዋ የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ ነው። ሥርጭቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 35 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት። መምሪያ ኀላፊው ባለፉት ወራት ለማኅበረሰቡ 36 ሺህ በላይ የወባ የምርመራ አገልግሎት መስጠት መቻሉንም ገልጸዋል። የክረምት ወቅትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን የወባ በሽታ ለመከላከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምክንያት የሚኾኑ አካባቢዎችን በማጽዳት፣በማፋሰስ የወባ በሽታን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባውም ገልጸዋል። የወባ በሽታ ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።

መምሪያው በተለይም በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከመደበኛው ሥራ በተጨማሪ “የድንገተኛ በሽታዎች መከላከል አስተግባሪ ቡድን” አቋቁሞ እየሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት። ማኅበረሰቡን የማስገንዘብ ፣ ውኃ የሚያቁሩ አካባቢዎችን ተከታትሎ የማፅዳትና ሌሎች የቅድመ መከላከል ሥራዎች መጀመራቸውንም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ ወባን መከላከል እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት። እንደ ጢስ ዓባይ ፣ወረብ እና ሌሎች በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የገጠር አካባቢዎች ሥርጭቱ ከፍ ያለ እንደኾነም አስገንዝበዋል። በኬሚካል እጥረት ምክንያት ርጭት እንዳልተደረገ የተናገሩት መምሪያ ኀላፊው ለማኅበረሰቡ የአጎበር ስርጭት በስፋት እየተዳረሰ ስለመኾኑ አስረድተዋል። ማኅበረሰቡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሃሳብ ወስዶ መተግበር፣ የወባ መከላከያ አጎበርንም በተገቢው መንገድ በመጠቀም ጤናውን መጠበቅ ይገባዋል ነው ያሉት። ማንኛውም የወባ በሽታ ምልክት የታየበት ሁሉ ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ መታክም እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢጋድ የሱዳን ችግር ፈች ኮሚቴ አቋቁሞ በአዲስ አበባ እንዲካሔድ አቅጣጫ ማስቀመጡ ታሪካዊ ውሳኔ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleበቀን ለ30 ህጻናት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የዓይን ህክምና ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።