
አዲስ አበባ: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ከሦስት ዓመታት በኋላ የተካሄደው መደበኛ የኢጋድ ስብሰባ ትልልቅ ውሳኔዎች የተላለፉበት ነበር ብለዋል።
በጉባዔው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ መሃማት ፣የአውሮፓ ኅብረት እና የሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከስብሰባው በተጨማሪ ከኬንያ፣ ከጅቡቲና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል ብለዋል።
እንደቃል አቀባዩ ገለጻ ኢጋድ አራት ሀገራት ያሉት ኮሚቴ በሱዳን ሰላምን ለማፈላለግ ወክሏል። ምክክር እና ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሔድ ተወስኗልም ነው ያሉት። በዚህ ሥራም መሪዎችን የማደራደር እና የሰብዓዊ ድጋፍ የማቀላጠፍ ሥራ ይከናወናል። ይህም ታሪካዊ የሚባል ውሳኔ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ። ተፋላሚ ኀይሎችን ለማስማማት የአራት ሀገራት መሪዎች ሚናቸውን እንዲወጡም ተወስኗል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚገኝበት አቅጣጫ የማመቻቸት ሥራም እንደሚሠራ ነው የተገለጸው።
ኤርትራም ከ16 ዓመታት በኋላ ወደ ጉባዔው መመለሷ ትልቅ ሚና ያለው እንደኾነም ነው የተነገረው። የኢጋድ አባል ሀገራት በሱዳን ጉዳይ የአቋም ልዩነት እንደሌላቸው ያሳዩበት ጉባዔም እንደነበር ነው ያስገነዘቡት። የኢጋድ ሚናና ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ሚናው እያደገ መምጣቱን አምባሳደር መለስ አንስተው ከእነዚህ መካከል በሱዳን እና በኢትዮጵያ የድንበር ይገባኛል ጉዳይ በናይሮቢ ምክክር እንዲደረግ የኾነው በኢጋድ ነው። በሶማሊያ እና በኬንያ መካከል በባሕር በር ይገባኛል የነበረባቸው ችግር የተፈታው እና በደቡብ ሱዳን ውስጥ የነበረው ችግር መፍትሔ ያገኘው በኢጋድ ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በሠራው ሥራም የኢጋድ ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየሁ የነበራቸው ሚና ትልቅ ነበር ነው ያሉት። በዚህም ምክንያት የመሪነት ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ በድጋሜ መመረጣቸውን አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን የኢጋድ አባል ሀገራት ሥራና ተግባርም ኾኖ መወሰዱን አስገንዝበዋል። አምባሳደር መለስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከተሳተፉበት በሳውዲ አረቢያ ከነበረው አሸባሪነትን የመዋጋት ጉባዔ ጎን ለጎን ከአሜሪካ እና ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ውይይት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡ በተለይ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት እርዳታን ማቋረጥ እና ላልተገባ ተግባር መጠቀም ጋር በተያያዘ ሰፊ ውይይት አድርገዋል ነው ያሉት። ተግባሩን ከማውገዝ በተጨማሪ አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ እንደሚሠራ ስምምነት የተደረሰበት ውይይት ነው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ እርዳታን ላልተገባ ተግባር መጠቀም ሕገወጥነት ነው ተጎጅዎችን ከመደገፍ አንጻር ከባድ ችግር የሚያመጣና የሚወገዝ ተግባር እንደኾነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚያምን ተናግረዋል። እስከአሁን ባለው አሀዛዊ መረጃ 33 ሺህ 260 የሚኾኑ ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ነው ያሉት። 22 ሺህ 600 የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ሱዳናውያን እና የሌላ ሀገር ዜጎች ናቸው። ኢትዮጵያም ሱዳናውያን ወደ ሦስተኛ ሀገር ለሚያደረጉት ጉዞ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለቪዛ የሚያወጡትን ወጪ እንደምታስቀርላቸው ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ፡- በአንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!