
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሽግግር ፍትሕ እና ሰላም ግንባታን የተመለከተ ሀገራዊ ጥናታዊ ውይይት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ የሕግ ምሁራን ጥናቶችን አቅርበዋል። በቀረቡ ጥናቶች ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ገድፍ የሀገራችንን ነባር እሴቶች በመጠቀም እና የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። የዛሬው ውይይት ዋና ዓላማም ሀገራችን ባሳለፈችው የጦርነት ወቅት የተከሰቱ ችግሮችን በሽግግር ፍትሕ በማረም ዘላቂ ሰላም መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ሀገር በቀል የኾኑ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሀገር በቀል የእርቀ ሰላም መንገዶችን እና ግልጽ ውይይቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል። መጀመሪያ በጦርነት ወቅት የወደሙ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ የሀገር ሀብቶችን ለይቶ መተማመን፤ በመቀጠልም ይቅርታ መጠያየቅ በመጨረሻም አጥፊ የነበረው አካል በሕግ ፊት ቀርቦ መጠየቅ እንዳለበትም ተገልጿል።
የሽግግር ፍትሕን በዚህ አካሄድ ተግባራዊ በማድረግ የወደሙ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ ለሀገርም ዘላቂ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል ነው የተባለው።
ከጥናት አቅራቢዎች መካከል የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ቀናው ተስፋየ የሽግግር ፍትሕ በዓለማችን ከ39 በላይ ሀገራት ጥቅም ላይ የዋለ የእርቀ ሰላም ሁነኛ መንገድ ነው ብለዋል። በሀገራችን የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ በማድረግ እውነትን ማውጣት፣ ተጎጅዎችን መካስ፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ይቅርታን ማውረድ እና የሀገርን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሕግ መምህሩ በኢትዮጽያ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ እንዲኾን ሁሉም ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል። በተለይም ምሁራን ጥናቶችን በመስራት እና ችግሮችን በመፍታት ከፍተኛ ሚና መጫዎት አለባቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!