
አዲስ አበባ: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ዓመታዊ ጉባዔ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲኾን ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ይህ ጉባዔ ከ300 በላይ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ መሪዎች ፣ ፖሊሲ አውጭዎችና አማካሪዎች ፣ የመንግሥትና የግል ተቋሞች፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ተወካዮች፣ የምጣኔ ሀብት ተንታኞችና ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ፣ የባንክና ኢንሹራንስ ከፍተኛ መኮንኖች ፣ የቴሌኮም ባለሙያዎች የሚገኙበት ነው። ሌሎችም አንቱ የተባሉ ቁልፍ በምሥራቅ አፍሪካና በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የፉይናንስ ተቋሞች የሚሳተፉበት፤ ሐሳብ የሚያዋጡበትና የሚከራከሩበት ታላቅ መድረክ መኾኑን የጉባዔው አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
በበይነ መረብ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በኬንያ ናይሮቢ የካፒታል ገበያ ደህንነት ባለሙያ ጆርጅ ኦዶንዶ ጉባዔው የአፍሪካን ጥቅም የሚያስጠብቁና የፋይናንስ ትስስር የሚያጠናክሩ ሐሳቦች የሚነሱበት ይኾናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመድረኩ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ማኅበራት ፕሬዚዳንት ያሬድ ሞላ ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ኢትዮጵያ ያላትን የመልማት እድልና በቀጣናው ያሉ እድሎችን አስተሳስራ መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ለዚህም ቁርጠኛ መኾኗን ተናግረዋል።
የዚህን ዓመት ጉባዔ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማኅበር (ኤሲሲኤ) አይ – ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት (ዘ-ካፒታል ኢንስቲቲዩት)፣ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት እና ኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ በኅብረት አዘጋጅተውታል ።
ለፖሊሲ አውጭዎችና አጥኝዎች የሚያግዙ የጥናት ውጤቶች እየቀረቡ እና ጥልቅ ውይይቶችም እየተካሄዱ ነው።
ጉባዔው የፊይናንስ ዘርፉንና የወደፊት ጉዞውን ይመለክታል፤ በዘርፉ ያሉትን ፖሊሲዎች፣ ሕግና ደንብ ለማጥራት አቅጣጫም ለመቀየስ እንደ ዓላማ ይዞ ተዘጋጅቷል።
የፉይናንስ አካታችነት ፣ የቀጣናው የኢኮኖሚ ጉዞና የኢትዮጵያ የአሁን መንገድ ፣ የካፒታል ገበያ ፣ የዲጂታል ፋይናንስ ጉዞ ፣ የፋይናንስ ገበያ ሊበራላይዜሽን ዙሪያ ያለው አጠቃላይ የፖሊሲ ውሳኔ እና ተግባራቸው በጉባዔው እየተፈተሸ ይገኛል።
ጉባዔው በሚያቀርባቸው ጥናቶች፣ በምርምር ሥራዎች፣ በፓናል ውይይቶችና ምክክሮች ለሀገር ቤት አጠቃላይ የፋይናንስ ጉዞ መፍትሔ ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።
በ6ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፉይናንስ ጉባኤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተጠሪ ኀላፊዎች፣ ኤክስፐርቶች ፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ ጉባዔውም ለ2 ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!