
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኤስ.ኤን.ቪ. የተባለ የኔዘርላንድ ግብረሰናይ ድርጅት በአማራና በትግራይ ክልሎች በጦርነት ለተጎዱ አከባቢዎች አራት ሺ 400 አርሶ አደሮች የሽንኩርት ምርጥ ዘር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ አማካሪ አቶ አብዱልሰመድ አብዱ ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለጹት፤ በሰሜኑ ግጭት ምክንያት በርካታ አርሶአደሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በመልሶ ማቋቋም ሥራ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። በኔዘርላንድ ግብረሰናይ ድርጅት በኩል የተደረገው ድጋፍም የመልሶ ማቋቋም ሥራውን የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኤስ. ኤን. ቪ. ግብረ ሰናይ ድርጅት ዳይሬክተር ጁሊ ግራሃም እንደተናገሩት፣ ድጋፉ በኤስ.ኤን.ቪ በሆርቲ ላይፍ ፕሮጀክት “የአርሶ አደሮች የማሳ ላይ ትምህርት ቤት” ታቅፈው የተሻሻለ የአትክልት ልማት አሠራር ለሚተገብሩ አራት ሺህ 400 አርሶ አደሮች የሚሰራጭ ሲሆን፤ 15 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሽንኩርት ምርት ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዘገባው የኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!