“የባሕር ዳር ጢስ ዓባይ መንገድ ፕሮጀክትን እስከ መስከረም 30 /2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት

99

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር ጢስ ዓባይ እየተገነባ ያለውን ደረጃውን የጠበቀ መንገድ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

ከባሕር ዳር ጢስ ዓባይ እየተገነባ ያለው ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልት መንገድ 21 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ለግንባታው 957 ሚሊዮን 930 ሺህ ብር በጀት ተይዞለታል፡፡ በአራት ዓመት ከስምንት ወር ለማጠናቀቅም ታቅዶ ነው እየተሠራ የሚገኘው፡፡ የመንገዱ የጎን ሥፋት 34 ነጥብ 5 ሜትር ይሸፍናል፡፡ መንገዱ የእግረኛ፣ የብስክሌት እና የመኪና መንገድን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡

መንገዱ ታኅሣሥ 2012 ዓ. ም ነበር የተጀመረው፡፡ የመንገዱ ዲዛይን የከተማ የአስፓልት መንገድ አሠራርን የተከተለ ነው፡፡ መንገዱን የሜልኮን ኮንስትራክሽን ነው እየገነባው የሚገኘው፡፡ የጎንድዋና ኢንጅነሪን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ የማማከር ሥራውን ይሠራል። በጀቱ ከፌዴራል መንግሥት የተገኘ ነው፡፡ መንገዱ ወደ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ የሚወስድ የ1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ለእግረኞች መጠቀሚያ ብቻ የሚኾን ደረጃውን የጠበቀ መንገድ እና ሁለት ተንጠልጣይ ድልድዮች እንዳሉትም ነው የተገለጸው።

በሜልኮን ኮንስትራክሽን የባሕር ዳር ጢስ እሳት የመንገድ ዲዛይን እና ግንባታ ሥራ ፕሮጀክት የፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጅነር ሰሎሞን ወልደ ገብርኤል የመንገዱ ግንባታ 40 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የአፈር ቆረጣ እና የሙሌት ሥራ፣ የውኃ ማፋሰሻዎች፣ መንገዱን አቋርጠው የሚያልፉ የመስኖ ቦዮች እና ባለ አራት ማዕዘን የውኃ መቀልበሻ ቱቦዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ወቅቱን ጠብቆ የወሰን ማስከበር ሥራ ባለመሠራቱ እና የዲዛይን ለውጥ በመኖሩ የተያዘለት የሦስት ዓመት የማጠናቀቂያ ጊዜ ወደ አራት ዓመት ከስምንት ወር ከፍ እንዲል መደረጉንም የፕሮጀክት አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ከዲዛይን ለውጥ በተጨማሪ የሲሚንቶ እጥረትና የግንባታ ጥሬ እቃ የዋጋ ጭማሪ ለመንገድ ሥራው መዘግየት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት፡፡

የባሕር ዳር ጢስ እሳት የመንገድ ዲዛይን እና ግንባታ ፕሮጀክት ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጅነር ሀብታሙ አስጨናቂ፤ ሥራው በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል። የባሕር ዳር ጢስ እሳት የመንገድ ዲዛይን እና ግንባታ ሥራ ፕሮጀክት የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ ከመንግሥት 10 በመቶ ጭማሪ ተደርጎለታል። ይኽም ፕሮጀክቱ የብድር አማራጭ እንዲያገኝ እንደረዳው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ መንገዱን እስከ መስከረም 30 /2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡የመንገድ ግንባታው ከዲዛይኑ ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢንጅነር ዮሴፍ የፕሮጀክቱ ዲዛይን 98 በመቶ፣ የአፈር ቆረጣ ሥራው 64 በመቶ፣ የውኃ መቀልበሻ ሥራው 10 በመቶ የተሠራ ሲኾን በዓባይ ወንዝ ላይ የሚሠራውን ተንጠልጣይ ድልድይ ጭምሮ 3 ድልድዮች እና አስፓልት የማልበሥ ሥራዎች በሚቀጥለው ዓመት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየሠራን ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ
Next articleበጦርነት ለተጎዱ ከአራት ሺህ በላይ አርሶአደሮች የምርጥ ዘር ድጋፍ ተደረገላቸው።