
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እና ለመንግሥት የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ያለመ የአማራና ኦሮሞ ምሁራን መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ታየ ደንድአ ‹‹ከተወያየንና ሐሳብ ከተለዋወጥን የማንፈታው ችግር የለም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአማራና ኦሮሞ አንድነት ለራሳቸው ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ለኢትዮጰያ አንድነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ አካላት አማራና ኦሮሞን ማጋጨት እንደሚፈልጉ ግልጽ መሆኑን በማመላከት ‹‹ይህ ከእናንተ ከምሁራን የተደበቀ አይደለም›› ብለዋል
‹‹ሕዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ሁሉ የሚነሱ አለመግባባቶችን ሁሉ ሥረ መሠረታቸውን ፈልጎ ማግኘት አስፈላጊ ነው›› ሲሉም አቶ ታዬ አሳስበዋል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ የሕዝቦችን የጋራ እሴት እና አንድነት የሚጠቅሱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን -ከአዲስ አበባ
ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው