
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ)መምሪያው የ2015 የትምህርት ዘመን ክልል አቀፍና ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን ስኬታማ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደብረ ማርቆስ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
በዚሁ መድረክ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ እንደገለጹት በ2015 የትምህርት ዘመን በዞኑ 35 ሺህ 357 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በ584 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በ60 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ 24 ሺህ 518 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ነው የገለጹት።
የፈተና አሰጣጡን በተሳካ መልኩ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን ያስረዱት መምሪያ ኀላፊው ኩረጃን በማስቀረት ተማሪዎች በጥሩ ሥነ ምግባር ፈተናውን እንዲወስዱና ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ይኸይስ ሀረጉ (ዶ.ር) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ኩረጃን ለማስቀረትና የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ተፈታኞችን ለማስተናገድና ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት በባለፈው ዓመት የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ዳግም እንዳይከሰት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት እያዘጋጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች የሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደር የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች፣ የፍትሕ፣ የትራንስፖርትና የፀጥታ ተቋማት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ።- ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!