
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል ባለ ድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ጥሪ አቀረቡ።
ሥራ አስፈፃሚው ሀብታሙ ውቤ በአሁኑ ወቅት በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
በመስመሮቹ ላይ እየተፈጸመ ያለው ስርቆት ለኅብረተሰቡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየተሠራ ላለው ሥራ ተግዳሮት ኾኗል ብለዋል። ተቋሙንም ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገው ይገኛል ብለዋል።
በስርቆቱ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ የቅንጅት ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይ መሰረተልማቶቹ የተተከሉባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ለፖሊስ እና ለመሥተዳድር አካላት መረጃ በመስጠትና እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ሀብታሙ ጠይቀዋል።
በማዕከላዊ ሪጅን 2 የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የጥገና ሥራ አስኪያጅ ጎሳዬ ደምሴ ስርቆት የሚፈጸምባቸውን ምሰሶዎች በመከታተል ጥገና ቢከናወንም ተደጋጋሚ ስርቆት ስለሚፈጸምባቸው ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ከብረታ ብረት ፋብሪካዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝቶ ችግሩን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት በማድረግ በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ አንስተው በቀጣይ ግን ከድርጅቶችና ችግሩ በስፋት በሚስተዋልበት አካባቢ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ውይይቱ እንደሚደረግ አቶ ጎሳዬ ጠቁመዋል።
የአፖሎ ስቲል የምርት ሱፐርቫይዘር ጌቱ ሞገስ እና የአቢሲኒያ ኢንቲግሬትድ ስቲል ፋብሪካ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ሔኖክ ደምሰው በሰጡት አስተያየት የተሰረቁ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌና የባቡር መሠረተ ልማቶች ወደ ማቅለጫ ፋብሪካ እንዳይገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ብረቶችን ለሽያጭ ወደ ፋብሪካ ይዘው የሚመጡ አካላትን ለሚመለከታቸው የሕግ አካላት አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ድርጅቶች ተሠርቀው የሚመጡ ብረቶችን ባለመግዛት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የብረት ፋብሪካዎች፣ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!