“የሌሎችን የማይፈልግ የራሱንም የማይሰጥ ሕዝብ ከምንም በላይ ለፍትሕ እና ለሕግ የበላይነት ምቹ ነው” የሕግ ባለሙያ

72

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ታሪክ እና እሳቤ ለብዙ ዘመናት በዘለቀው ዘውዳዊው ሥርዓት ጅማሮዎች ቢኖሩትም ለዘመናት የዘለቀው የዘውዳዊው ሥርዓት አክትሞ የደርግ መንግሥት መንበረ መንግሥቱን ሲቆጣጠር መሠረቱ መጣሉን የተለያዩ ጸሐፍት ይጠቅሳሉ። ከዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ትውውቅ ማግስት መቀንቀን የጀመረው የዘውግ ፖለቲካ በሀገሪቱ ጥንታዊ እና ታሪካዊ አብሮነት ውስጥ ቅርቃር መሆን ጀመረ ሲሉ የሚሞግቱ የዘርፉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ውብ በሆነው ልዩነት እና ሕብረ ብሔራዊነት መካከል ጭራ እየሰነጠቁ እና ጥግ እያበጁ የሚሸጎጡ ደካማ ፖለቲከኞች አብሮ ለኖረው ሕዝብ ደንቃራ ሆኑበት፡፡

ምንም እንኳን ከቅድመ ደርግ የሚመዘዝ የፖለቲካ ቁርሾ እና መነሾ ያላቸው ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ቢኖሩም የልዩነት እና የጥላቻ ፖለቲካ ዘር ከደርግ መንግሥት መመሰረት ጀምሮ በግልጽ መታየት እንደጀመረ ይነገራል፡፡ አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ የዶናልድ ሊቨንን የታሪክ መጽሐፍ “ትልቋ ኢትዮጵያ፡ የብዙ ነገዶች ማሕበረሰብ” በሚል ርዕስ 2007 ዓ.ም ላይ በተረጎሙት መጽሐፋቸው የዘውግ ፖለቲካ በዘመነ ደርግ የተለያዩ የፓለቲካ እሳቤዎች እና ልዩነቶችን መሠረት አድርጎ ያቆጠቆጠበት ወቅት ነበር ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ባለፉ የቅርብ መንግሥታት ደግሞ ዘውገኝነት መለያ እና መንግሥታዊ መዋቅር የተዘጋጀለት የፖለቲካ መዘውር ሆኗል ይላሉ፡፡

መንግሥት ወርዶ መንግሥት ሲተካ የእኔ የሚለውን እያስጠጋ እና በእኔ ላይ ይመጣል የሚለውን ደግሞ እያሳደደ መቀጠል ዕጣ ፋንታ እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ በመንግሥት ላይ የሚመጣ በዐይኔ መጣ የሚሉ ታማኝ ደጋፊዎች እና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እስካለ ድረስ ህልውናየ አይቀጥልም ብለው የሚያስቡ ሞጋቾች የሚፈጥሩት ግጭት ውሎ ሲያድር አደገኛ ግጭት እስከመሆን የደረሰበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ተደጋግሞ የታየው ከባድ ፈተናም ወደ ጦርነት መግባት ሳይሆን ድህረ ጦርነትን ያለቅራኔ መቋጨት ነበር፡፡

ከግጭቶች እና ጦርነቶች በኋላ ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የሚነሳው ዘላቂ ግጭትን ለማቆም፣ ያጋጠሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ወንጀሎችን በምን መልኩ ምላሽ ይሰጣቸው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ድህረ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመከሩ የዳኝነት ሥርዓቶች መካከል የሽግግር ፍትሕ ቀዳሚው ነው፡፡ በርካታ ሀገራት ጦርነቶችን በበላይነትም ሆነ በሠላም ከፈቱ በኋላ የተገኘውን አንጻራዊ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የሽግግር ፍትሕን እንደ ሁነኛ አማራጭ ይጠቀማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከልምድ፣ ከመንግሥታት ጣልቃ ገብነት እና ከተለያዩ ችግሮች አንጻር ተገቢውን ውጤት አምጥቷል ባይባልም የሽግግር ፍትሕ የተጀመረባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ይነገራል፡፡

የሽግግር ፍትሕ አስከፊ ግጭት፣ ጭቆና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ተከትሎ ተጠያቂነትን፣ ፍትሕን እና እርቅን በማረጋገጥ ዘላቂ ሠላም የሚፍጥር የዳኝነት ሥርዓት እንደሆነ አሚኮ ያነጋገራቸው የሕግ አማካሪው አቶ አደራው አዲሱ ይገልጻሉ። የሽግግር ፍትሕ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የፍትሕ ሥርዓት በመሆኑም ጥንቃቄ የሚያስፍገው እንደሆነ የሕግ ባለሙያው በአጽንዖት ይገልጻሉ፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትሉ ግጭቶች ይፈጠራሉ የሚሉት የሕግ ባለሙያው የሽግግር ፍትሕ ግጭቶቹን አርሞ፣ ፍትሕን አስፍኖ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ አድርጎ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደ ሚገነባበት ሠላማዊ ሁኔታ ለመሸጋገር የሚደረግ ሂደት ነው ይላሉ። የሽግግር ፍትሕ የታለመለትን ሠላማዊ ሽግግር እንዲያመጣ ግን አሳታፊ መሆን ይኖርበታል ተብሎ ይታመናል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን አውዳሚ ጦርነት ተከትሎ ችግሩን መፍትሄ ሰጥቶ ለመቋጨት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ የሲቪክ ተቋማት የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ እንዲኖር ሲጠየቅ መቆየቱን ያነሱት የሕግ ባለሙያው ሂደቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ቀናዒነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ የወጣቶችን፣ የፖለቲካ ልሂቃንን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ የመንግሥትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት የአማራ ሕዝብ በ1987 ዓ.ም የሀገሪቷ ሕግ መንግሥት ሲጸድቅ የተፈጠረው ዓይነት ችግር እንዳይደገም ሂደቱን መከታተል፣ በቅንነት ማየት፣ በዕውቀት መሞገት እና በብስለት መራመድ ይኖርበታል፡፡ በተለይም የፖለቲካ እና የሕግ ዕውቀት ያላቸው የማሕበረሰብ አንቂዎች በስሜት ከመራመድ ይልቅ ነገሮችን በስሌት ማየትን መልመድ ይኖርባቸዋል፤ ሕግ ዕውቀት እና ጥበብን ይጠይቃል የሚሉት ባለሙያው በደቦ መመልከት የሕግ ርትዕን አያመጣም፤ ፍትሕንም አያሰፍንም ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ለሕግ ልዕልና የተለየ ዕይታ ያለው ሕግ አዋቂ ሕዝብ ነው የሚሉት አቶ አደራው የአባቶችን ጥበብ ተጠቅሞ ችግሮችን መሻገር መለማመድ አለብን ብለዋል፡፡ የሌሎችን የማይፈልግ የራሱንም የማይሰጥ ሕዝብ ከምንም በላይ ለፍትሕ እና የሕግ የበላይነት ምቹ ነው። የአማራ ሕዝብ ከዚህ አንጻር ከታየ ደግሞ የዳበረ ልምድ እና ሀገር በቀል ዕውቀት ያከማቸ ነው ብለዋል፡፡ ያንን ልምድ እና ዕውቀት መጠቀም ደግሞ የዚህ ዘመን ትውልድ ድርሻ መሆኑን በመግለጽ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጣ ፡ ግንቭት 30/2015 ዓ.ስ
Next articleፋብሪካዎች ተሠርቀው የሚመጡ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶችን ባለመግዛት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ