
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመኮይ ግርማ ወንድአፍራሽ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ ከፍተኛ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡
ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት ተማሪዎች ጥቂት ነበሩ፡፡
ይህ ውጤት ቁጭት ፈጥሮብናል ያሉት የትምህርት ቤቱ የእንግሊዘኛ መምህር አብዱ ጋሻው እና የሂሳብ መምህር ሻምበል ባዩ መምህራን እና ተማሪዎች ውጤቱን በመጭው ሀገር አቀፍ ፈተና ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠሩ ስለመኾናቸው ነው የተናገሩት፡፡
መምህራኑ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በቤተ ሙከራ፣ በክለሳ ትምህርት፣ ጥያቄዎችን አዘጋጅቶ ለተማሪዎቹ በመስጠት እና ተከታታይነት ያለው ምዘና በማድረግ ተማሪዎችን ለማብቃት እየሠሩ እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡
ተማሪ የአብስራ ስዩም፣ ተማሪ ቢኒያም ደበበ እና ተማሪ ሀና ሀብታሙ ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ በኢንተርኔት የታገዘ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እንደተመቻቸላቸው ተናግረዋል፡፡
መምህራንም በሥነ ልቦና እና በዕውቀት በቂ ዝግጅት እንዲኖር እየረዷቸው እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ተሾመ አውላቸው ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን ክብር ለመመለስ በቁጭት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
የወረዳው አሥተዳደርና የይፋት ልማት ማኅበር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉና ከትምህርት ተቋሙ ጋር በቅንጅት እየሠሩ ስለመኾናቸውም ርዕሰ መምህር ተሾመ ተናግረዋል::
በዚህም እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች በመነሳት በትምህርት ዘመኑ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡
በወረዳው በሚገኙ ሁለት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ የሚገኙ 602 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በመጭው ሐምሌ ወር የሚሰጠውን ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ በቂ ዝግጅት እያደረጉ ስለመኾናቸውም ከወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ:- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!