“ውይይቱ በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰላምን ለማስፈን መሰረት የጣለ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

140

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራና የትግራይ መስተዳድሮች ውይይት በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰላምን ለማስፈን መሰረት የጣለ መሆኑን የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለጹት፤ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ቁሳዊ፣ ሰብአዊና ስነልቦናዊ ጉዳት አድርሷል፤ ከጦርነት አትራፊ ወገን የለም ብለዋል።

የጦርነት የመጨረሻ መቋጫው የሰላም ድርድር በመሆኑ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሰላም ወርዶ ህዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።

ስምምነቱ መሬት እንዲነካና ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ካስፈለገ የሁሉም ወገኖች መልካም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ፤ የሰላም ስምምነቱን መሬት ለማውረድ ሰኔ 3/2015ዓ.ም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የመሩት ልዑክ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳዎች የህዝብ ተወካዮች አባላት ባሉበት በባህር ዳር ከተማ ውይይት አድርገዋል።

ዋና ዓላማው መሪዎችን ከመሪ በማገናኘት የተጀመረውን ሰላም ማጽናትና ትክክለኛ ሰላም መሬት ላይ እንዲወርድ ማስቻል ነው።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች ለዘመናት ተዋልደውና ተጋምደው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ወደፊትም በጋራ መኖራቸው አይቀሬ በመሆኑ የበለጠ ለማጎልበት ሰላሙን ለማዝለቅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉ አለመግባባቶች የህዝብን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ በህግ ማዕቀፍ መፈታት አለበት።

ይህም ለህዝብ ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ሲባል የሚደረግ ግንኙነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በውይይቱ ወቅት ለሰላም በራችን ክፍት ነው፤ ሁልጊዜም ለሰላም አማራጭ የክልሉ መንግስት ቅድሚያ ይሰጣል ሲሉ መናገራቸውን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ግንኙነቱ ከልብ መሆኑ ማስገንዘብ ተችሏል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ለሰላም መስፈን የትኛውንም ዋጋ መክፈል እንደሚያስፈልግ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳም የትግራይ ህዝብ ጦርነት የሰለቸው ህዝብ በመሆኑ የጥይት ድምጽ መስማት እንደማይፈልግ መናገራቸውን አቶ ግዛቸው ጠቁመዋል።

የተጀመሩ መልካም ግንኙነቶች በየደረጃው አመራር እየተደገፉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ወደቀድሞው ለመመለስ መግባባት ላይ የተደረሰበት ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በትጥቅና በጠመንጃ የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በህግ፣ በውይይትና በንግግር ለመፍታት ቁርጠኝነቱ በሁለቱም ክልል አመራሮች እንዳለ መገለጹን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው፤ በሁለቱም ክልሎች በኩል በጦርነት የወደመውን ንብረት፣ መሰረተ ልማት መጠገን፣ የህዝቡን የስነ ልቦና ስብራት መመለስ፣ አካባቢውን የበለጠ ሰላም እንዲሆን ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ አብራርተዋል።

የተደረገው ግንኙነት የተጀመረውን ሰላም የበለጠ መሬት በማውረድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትልቅ መሰረት የጣለ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አቶ ግዛቸው፤ ግንኙነቱ የመጨረሻ ሳይሆን በቀጣይ በየደረጃው ባለው አመራር ተደግፎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይቀጥላል።

ግንኙነቱን በማጠናከር በተገቢው ሁኔታ ያልተጀመሩ የየብስ የትራንስፖርት አገለግሎቶች በመደበኛነት እንዲጀመሩ፣ የንግድና የማህበራዊ እንቅስቃሴው ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ በሁለቱ ክልሎች መካከል መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ዘገባው የኢፕድ ነው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትምህርት ቤታችንን ክብር የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጀን ነው” ተማሪዎች
Next articleኽምጠ ዊከ ጋዜጣ ፡ ግንቭት 30/2015 ዓ.ስ