የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡

245

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) በ16 ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ነገ ከቀኑ በ9፡00 በተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ነው የሚጀመረው፡፡ ስሑል ሽረ ከኢትዮጵያ ቡና በትግራይ ስታዲዬም የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ሰኞ ከቀኑ 9፡00 ይከናወናል፡፡

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች የአማራ ክልል ተወካዮቹ ፋሲል ከነማ እና ባሕር ዳር ከነማ ከሜዳቸው ውጭ ይጫወታሉ፡፡ የኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በቅርቡ ያነሱት አጼዎቹ ወደ አዳማ አቅንተው በአበበ ቢቂላ ስታዲዬም ከአደማ ከነማ ይጫወታሉ፡፡ የጣናው ሞገድ ደግሞ ከጂማ አባ ጅፋር ይገናኛል፤ ነገር ግን ጂማ አባ ጂፋሮች ያለፈው ዓመት የዞረ ቅጣት ስላለባቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ ነው የሚካሄደው፡፡

ዓፄቹ ዛሬ በአዳማ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሠርተው የነገውን ጨዋታ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጨዋታ መርሀ ግብር የጂማ አባ ጂፋርና የባሕር ዳር ከነማ ጨዋታ እሑድ ከቀኑ 9፡00 ጂማ ስታዲዬም እንደሆነ ቢያሳይም ውድድሩ ግን ሰኞ በአደማ አበበ ቢቂላ ስታዲዬም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት ‹‹ዛሬ አዳማ ላይ የመጨረሻ ልምምድ ሠርተናል፤ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የነበረን ድንቅ ጨዋታና ውጤት ለነገውም ስንቅ ሆኖናል፡፡ በጥሩ የማሸነፍ ስነ ልቦና ላይም እንገኛለን›› ብለዋል፡፡ በባሕር ዳር ሲያደርጉ የነበረው ዝግጅትም መልካም እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጉዳት ካጋጠመው እንየው ካሳሁን በቀር ሌሎች ተጫዋቾች በመልካም ጤንነትና ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚገኙም አሰልጣኝ ስዩም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት የነበረንን ጠንካራ ተፎካካሪነት ለማስቀጠል በቂ ዝግጅት አድርገናል›› ብለዋል አሰልጣኙ፡፡

ፎቶ፡- ከፋሲል ከነማ ማኅበራዊ ገጽ

Previous article“ስታዲዬሙ ውድድሮችን ለማስተናገድ በካፍ የተጠየቀውን መስፈርት ማሟላቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና የካፍ ተወካዮች በቦታው ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡” የወልድያ ከተማ አስተዳድር
Next articleበኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በደረሰ ስርቆት እና ጉዳት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱን የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡