የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አርማ የታተመባቸውን የኪስ ቦርሳዎች በማዘጋጀትና መታወቂያ በማስመሰል ለሕገወጥ ተግባራት ጥቅም ላይ ለማዋል ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

198

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው የተቋሙ አርማ የታተመባቸውን የኪስ ቦርሳዎችን ወይም ዋሌቶችን በማዘጋጀትና መታወቂያ በማስመሰል ለሕገ ወጥ ተግባራት ጥቅም ላይ ለማዋል ሙከራ ሲያደረጉ የነበሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንና ኅብረተሰቡም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አክሎም፤ በዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦች የተቋሙ አርማ የታተመባቸውን የኪስ ቦርሳዎችን ወይም ዋሌቶችን መታወቂያ አስመስለው በማዘጋጀት በተለያዩ አካባቢዎች ለማሰራጨት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበርና ካዘጋጇቸው የኪስ ቦርሳዎች ውስጥ የተወሰኑት በአንዳንድ ግለሰቦች እጅ እንደገቡ መታወቁን አመልክቷል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የተቋሙ አርማ የታተመባቸውን የኪስ ቦርሳዎች እንደ መታወቂያ በማሳየት በሕገወጥ ተግባር መሰማራታቸውንና በተቋሙ ስም ያለአግባብ አገልግሎት ለማግኘት ሙከራ እያደረጉ መሆኑ እንደተደረሰበትም አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ እንዳመለከተው፤ የተቋሙ አርማ የታተመበትን የኪስ ቦርሳ ወይም ዋሌት ይዞ መገኘት ብሎም ሕገወጥ ለሆነ ተግባር ማዋል ሕጋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ይህ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አርማ የታተመበት የኪስ ቦርሳ በእጁ የገባ ግለሰብ በአካባቢው ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ እንዲያስረክብ ወይም በስልክ ቁጥሮች 0115543681 እና 0115543804 በመወደል እንዲያሳውቅ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ ይህን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብም በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ ያሳውቃል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተፈናቅለው ለተመለሱ የአብርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች ለእርባታ የሚያገለግሉ እንሰሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡
Next articleለደቡብ ወሎ ዞን የፋይናንስ ተቋማት ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የቢሮ መገልገያ ቁሶች ድጋፍ ተደረገ።