ተፈናቅለው ለተመለሱ የአብርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች ለእርባታ የሚያገለግሉ እንሰሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡

98

ሰቆጣ: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ቆይተው ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ለ32 የአብርገሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ለእርባታ የሚያገለግሉ የፍየል ድጋፍ ተደርጓል። ድጋፍ የተደረገው ፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ በተባሉ በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪነት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ድጋፍ መኾኑ ተገልጿል፡፡ 192 የእርባታ ፍየሎች ናቸው ተገዝተው ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ተፈናቃዮች የተሰጡት።

በባለፈው ሳምንት በዚህ በጎ አድራጊ አማካኝነት ከሰቆጣ ከተማ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለመጡ ወገኖች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ዱቄት ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል።ፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁን ወክለው ድጋፉን ያስረከቡት አቶ ማራቸው ሙጩ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ያግዝ ዘንድ 1 ሚሊዮን 920 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ 192 የእርባታ ፍየሎችን ገዝተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው 14 እማወራዎችና 18 አባወራዎች መኾናቸውንም ነው ያብራሩት። ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምም የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ማራቸው ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ለአሚኮ እንደገለጹት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውንና ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ኀላፊው በዚህም በአበርገሌ ወረዳ 32 እማወራና አባወራዎችን መልሶ ለማቋቋም ለእያንዳንዳቸው 6 የእርባታ ፍየሎች በፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ አማካኝነት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። አቶ ምህረት የተደረገው ድጋፍ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ንብረት እንዲያፈሩና ከተረጂነት እንዲላቀቁ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ቀጣይም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለእርሻ ግብዓት የሚያገለግሉ በሬ፣ ማዳበሪና ምርጥ ዘር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በወረዳው የ03 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ አባዲ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት 26 ከብቶች፣ 18 የንብ ቀፎና የመኖሪያ ቤታቸው ጉዳት እንደደረሰበት ነው የተናገሩት።

“በጦርነቱ ምክንያት እኔም ከቤት ንብረት ተፈናቅዬ ከሁለት ዓመት በላይ በመጠለያ ጣቢያ ኖሪያለሁ” የሚሉት አቶ ሞገስ አሁን ወደ ቀያቸው ቢመለሱም ለችግር እንደተጋለጡ ነው ያስረዱት። ዛሬ ለእርባታ የሚውሉ ፍየሎች ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸው ድጋፉ በጦርነቱ ምክንያት ያጡትን ንብረት መልሶ ለመተካት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። አርሶ አደር ነይኑ ገብረመስቀል በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ያላቸውን እንስሳት በረሃ ጥለው ሰላም ፍለጋ ተፈናቅለው በወለህ መጠለያ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ የራሳቸውን ሀብት ለማፍራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። የተደረገላቸውን የፍየል ድጋፍ መሰረት በማድረግ ወረዳቸው ለእንስሳት እርባታ ምቹ በመኾኑ የራሳቸውን ሀብት ለማፍራት እንደሚጠቀሙበት አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋማ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።
Next articleየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አርማ የታተመባቸውን የኪስ ቦርሳዎች በማዘጋጀትና መታወቂያ በማስመሰል ለሕገወጥ ተግባራት ጥቅም ላይ ለማዋል ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ