ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋማ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።

53

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመልሶ ማቋቋም ግንባታ ፕሮግራም የሚውል የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መርሃ-ግብር ይፋ ሆኗል።
በግጭት ምክንያት የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የተባበረ ጥረት ያስፈልጋል ተብሏል። የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና መገንባት የጥናት ውጤት ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመልሶ ማቋቋም ግንባታ ፕሮግራም የሚውል የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል። የዳሰሳ ጥናቱ በሸፈናቸው ክልሎች በማኅበራዊ፣ በምርት፣ በመሠረተ-ልማት እና ባለብዙ ዘርፎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውድመት መድረሱም ተጠቁሟል። የምክክር መድረኩ ዓላማ በተለያዩ ግጭቶች የደረሰውን ጉዳትና መልሶ ማቋቋም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ምክክር በማድረግ ሰው ተኮር ልማትን በማጠናከር ግንኙነትን ለማደስ እንደሆነ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጦርነቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚሰጡ ተቋማትና መሠረተ-ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡ በጦርነቱ የደረሰውን የውድመትና የኪሳራ መጠን ለመለየትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ጥናት ተካሂዶ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥትና ከልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። በጦርነቱ የደረሰውን ከፍተኛ ውደመት በዘላቂነት ለመገንባትም የልማት አጋር ድርጅቶችና ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የዓለም ባንክ፣ በተመድ የልማት ፕሮግራም፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች አጋር የልማት ተቋማት ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመልሶ ግንባታ ሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ መንግሥት በዓለም ባንክ እና በልማት አጋሮች የቴክኒክ ድጋፍ ግጭቱ ያደረሰውን ውድመት፣ ጥፋት እና የፈጠረውን ፍላጎት አካታች መረጃ ለመስጠት የጉዳት ፍላጎት ግምገማ ማድረጉም ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ2 ሺህ በላይ የልጅነት ጋብቻዎች ከተጋቢ ቤተሰቦች ጋር በተደረገ ድርድር ማስቆም ተችሏል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ
Next articleተፈናቅለው ለተመለሱ የአብርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች ለእርባታ የሚያገለግሉ እንሰሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡