“ከ2 ሺህ በላይ የልጅነት ጋብቻዎች ከተጋቢ ቤተሰቦች ጋር በተደረገ ድርድር ማስቆም ተችሏል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

73

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴት ልጅ ግርዛትና የሕጻናት ጋብቻ ለመከላከል በሚቻልባቸው ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የሴት ልጅ ግርዛትና የሕጻናት ጋብቻን ለመከላከል በሚቻልባቸው ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎችና በቀጣይ መሠራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቧል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መልዓከሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በመጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሴት ልጅ ግርዛት የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩን አንስተዋል። በመጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለን ነገር መፈጸም ደግሞ ሰዎችን ለሌላ ችግር ማጋለጥ ካልኾነ በስተቀር ተቀባይነት እንደሌለው አንስተዋል።

በክርስትና ሃይማኖት ተጋቢዎች ለአካለ መጠን ሳይደርሱ የሚፈጸም ጋብቻም ሃይማኖታዊ አስተምህሮው እንደማይፈቅድ ነው ያነሱት። ችግሩን ለመቅረፍ በሃይማኖታዊ ተቋማት ትምህርት እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።

ሼህ አብዱረህማን ሡልጣን እንዳሉት ደግሞ ጋብቻ ክቡር እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲፈጸም አሏህ ማንኛውንም የሰው ልጅ አዝዟል። ጋብቻ ሲፈጸም ደግሞ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በጠበቀ መንገድ መፈጸም እንዳለበት አንስተዋል። ማንኛውንም የሰውን ልጅ የሚጎዳ ድርጊት በሙሉ እምነቱ እንደሚከለክል ያነሱት ሼህ አብዱረህማን በቀጣይ ስለ ጎጅ ድርጊቶች ማስተማር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከ18 ዓመት በታች የኾነ ማንኛውም ሰው ጋብቻ ቢፈጽም ሕገ ወጥ እንደኾነ በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 647 እና 648 መደንገጉን ያነሱት ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ የሥራ ሂደት ባለሙያ ሙሉዓለም ሻረው ናቸው። ባለሙያው እንዳብራሩት የልጅነት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት በአማራ ክልል በስፋት ከሚከናወኑ ጎጅ ድርጊቶች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህን ጎጅ ድርጊቶች ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።

በ2015 ዓ.ም 9 ሺህ 900 የልጅነት ጋብቻ ጥቆማዎች ከማኅበረሰቡ ቀርበዋል። ከዚህ ውስጥ ከ2 ሺህ በላይ የሚኾኑት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በተደረገ ድርድር ማስቆም ተችሏል። ከ7 ሺህ በላይ የሚኾኑት ደግሞ ለጋብቻ እድሜያቸው የደረሱ ኾነው በመገኘታቸው ጋብቻ ፈጽመዋል። 1 ሺህ 500 በድብቅ ጋብቻ በፈጸሙ ሰዎች ላይ ደግሞ በሕግ መፍትሔ እንዲያገኝ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኞች የሴት ልጅ ግርዛት እየቀነሰ መምጣቱን ባለሙያው ገልጸዋል። በቀጣይም ጎጅ ድርጊቶችን ለመከላከል የፍትህ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማት ትኩረት መሥጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምድሪቷ ሕይዎት!
Next articleግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋማ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።