የምድሪቷ ሕይዎት!

65

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለደንም ጊዜ አለው፡፡ ደንም እንደ ሰው ልጅ ነገሥታት በተቀያየሩ እና መንግሥታት በተለዋወጡ ጊዜ ክፉ እና ደግ ጊዜያትን ያሳልፋል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ደን ከሰው ልጅ ጋር በርካታ ውጣ ውረዶችን አይቷል፡፡ ብዙ ዘመናትን ሳንርቅ አንድ ወቅት 40 በመቶ የቆዳ ስፋቷ በደን የተሸፈነ ነበር የምትባለው ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗ አስፈሪ በሆነ ደረጃ ወርዶ ሦስት በመቶ ድረስ አሽቆልቁሎ እንደነበር የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡

ደን የምድሪቷ ሕይዎት ነው፡፡ አረንጓዴ የለበሰ ምድርን ማየት የነፍስ ሃሴት እንዳለው ሁሉ ለምድሪቷም ጸጋ መልበስ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ጨምሮ በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጡራን ሁሉ የሚተነፍሱት አየር የደን ውጤት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስለደን ስንነጋገር እና ስናስብ ስለምንተነፍሰው አየር እየተጨነቅን እንደሆነ ማሰብ ይገባል ሲሉ የደን ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ለዚያም ይመስላል የደን መመናመንን እና የኢንዳስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እስከመሆን የደረሰው፡፡

የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ነገሥታት ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ቁርኝት እጅግ አስገራሚ ነው ቢባልም ከደን ጋር የተቆራኘ ታሪክ ያላቸው ነገሥታት ታሪክ የሚጀምረው ግን ዘግይቶ ነው፡፡ ከ1434 ዓ.ም እስከ 1468 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን የመሩት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ሽዋ አካባቢ በአንኮበር እና ጣርማ በር መካከል ከሚገኘው የወፍ ዋሻ ደን የሃበሻ ጥድ ዘር ተለቅሞ በአካባቢው እንዲሰፋፋ አድርገዋል ይባልላቸዋል፡፡ በተጨማሪም የተለቀመው የደን ፍሬ ከአዲስ አበባ ቅርብ እርቀት ላይ በሚገኘው እና በወቅቱ ተራቁቶ የነበረው የመናገሻ ሱባ ደን እንዲለማ አድርገዋል፡፡ ሁለቱ ደኖች የንጉሠ ነገሥቱ ጥብቅ ደኖች እንደነበሩም ይነገራል፡፡

የደን ባለሙያዎች ከዘርዓ ያዕቆብ የደን ልማት በጎ ተግባር በዘለለ ከደን ጋር ተያይዞ የሚነሳው የነገሥታቱ ታሪክ ብዙም አስተማሪ ሆኖ አይገኝም ይላሉ፡፡ ነገሥታቱ በየጊዜው ከቦታ ቦታ መናገሻቸውን እና መዲናቸውን ከመቀየራቸው ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ጥብቅ ደኖች ይጨፈጨፉ ነበር፡፡ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ተደጋጋሚ ጦርነቶች፣ የእርሻ ቦታ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች የሀገሪቷን የደን ሽፋን እጅግ ዝቅ አድርገውት እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁን ያለው የደን ሽፋን ፈጽሞ እንዳይጠፋ የታደገው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከባሕር ማዶ አስመጥተው ያላመዱት የባሕር ዛፍ ተክል መስፋፋቱ ነው ይባላል፡፡

ስለደን ስንነጋገር ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አብረው ይነሳሉ የሚሉት በአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ባለስልጣን የተፈጥሮ ደኖች ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አካሉ ናቸው፡፡ ተፈጥሯዊ ደን እና ሰው ሰራሽ ደን በሚል ለይቶ መመልከት እንደሚገባ የሚያነሱት ዳይሬክተሩ ተፈጥሯዊ ደኖች አሁንም ድረስ እየተመናመኑ ነው ይላሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት የተሰጠው ሰው ሰራሽ ደን ደግሞ መሻሻሎች ይታዩበታል ይላሉ፡፡ በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም አሁናዊው የሀገሪቷ የደን ሽፋን ወደ 10 በመቶ አካባቢ ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ሰው ሰራሽ ደን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሸሎች እንዳሉት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ያለው የደን ሽፋን ከሀገሪቱ የደን ሽፋን አንጻር ሲታይ ብዙም የተለየ አይደለም የሚሉት አቶ ተፈራ አሁናዊው የክልሉ የደን ሽፋን ከ12 እስከ 15 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ክልሉ በየዓመቱ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማውጣት የሚያስጠብቃቸው 18 የሚደርሱ የመንግሥት ጥብቅ ደኖች አሉ፡፡ በአምስት ዞን እና በ21 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጥብቅ ደኖች ለሌሎች አካባቢዎችም ለማስተማሪያነት እንደ ተሞክሮ የሚወሰዱ ናቸው ይላሉ ዳይሬክተሩ፡፡

በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ደኖች በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ያሉ ናቸው ያሉን አቶ ተፈራ አሁንም ዘርፈ ብዙ አደጋዎች ተደቅነውባቸዋል ይላሉ፡፡ ደኖቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለአልሚዎች የሚሰጡ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች የደኖቹ የህልውና ስጋት እየሆኑ መጥተዋል ፤ ለሰው ሰራሽ ደን የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ለተፈጥሮ ደን ልማት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ተፈራ አካባቢዎቹን ከሰው እና እንስሳት ንክኪ መከለል፣ ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ ብቻ ይበቃል ይላሉ፡፡ የተፈጥሮ ደኖን ያለባቸው አካባቢዎች በውስጣቸው በቂ ዘር እና ስር ስላላቸው በቀላሉ የሚያገግሙ በመሆናቸው የተለየ ጥረትን እንደማይጠይቁ ገልጸዋል ፡፡

የተፈጥሮ ደኖችን ለመጠበቅ ሕዝብ እና መንግሥት መናበብ ይኖርባቸዋል፡፡ የፍትህ እና የጸጥታ አካላት የወጡ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ማስፈጸም፣ የመሬት ቢሮ ጥብቅ የደን ቦታዎችን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት፣ የልማት ደርጅቶች ዘርፉን መደገፍ እንዲሁም ግብርና የጉዳዩን ጥቅም እና አስፈላጊነት በመረዳት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ይላሉ አቶ ተፈራ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን የተሻለ እና ጠንካራ ለማድረግ የረጅ ድርጅቶች እና ሀገራዊ ተቋማት ትብብር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
Next article“ከ2 ሺህ በላይ የልጅነት ጋብቻዎች ከተጋቢ ቤተሰቦች ጋር በተደረገ ድርድር ማስቆም ተችሏል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ