
አዲስ አበባ : ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ .አይ.ዲ) በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን እና በሽታ የመከላከል አቅምን ለመገንባት የሚያስችል የ12 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እና የፕሮጀክት ትግበራ ይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል።
ፕሮጀክቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽን ለማጠናከር በአማራ፣ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተመረጡ 12 ወረዳዎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የሚተገበር ሲኾን የኅብረተሰቡን የጤና ችግር ለመፍታትና ከባድ የጤና ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዓላማ ያደረገም ነው።
የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) ሚሽን ዳይሬክተር ቲመቲ ስቴን አንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩኤስ ኤይድ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ ከችግር ለማገገም እና ፈጣን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን ለመገንባት ድጋፍ ተደርጓል። የኢትዮጵያም የዚህ አካል ነው ብለዋል።
“እኛም ኢትዮጵያውያን ጤናማ እና የተሻለ ህይዎት እንዲኖሩ ድጋፍ ማድረግ ስለቻልን ደስተኞች ነን” ነው ያሉት። የፕሮጀክቱ ትግበራ ደግሞ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በቀይ መስቀል ማኅበር እና በጤና ሳይንስ አሥተዳደር በኩል የሚከወን መኾኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ደ.ር) በበኩላቸው “የጤና ሥርዓታችን ጠንካራ አንዲኾን ሥትሠሩ የነበራችሁ በዚህ ድጋፍ አንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኃላ የኮሮና ወረርሽኝ የጤና ሥርዓታችን ምን ያክል ቀድሞ ሊደራጅ አንደሚገባ ያስተማረን ነው” ብለዋል። የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ፕሮጀክት በሀገር ደረጃ ሳይኾን በወረዳ ደረጃ የሚተገበር መኾኑ ለኅብረተሰቡ ለመድረስ የሚያግዝ ጥሩ አጋጣሚ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የጤና ሙያተኞች ስልጠና ማግኘት አንዲችሉ እና አቅምን ለማጎልበት እንደሚረዳም አስገንዝበዋል። ፕሮጀክቱ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ መቻሉ ሌላው ጠቀሜታው እንደኾነም አብራርተዋል።
“የጤና ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ ፈጣን የአደጋ ምላሽ መስጠት አንዲችል ለማድረግ፣ የማኅበረሰብ የጤና ችግሮችን ካሉበት ሁኔታ ለማውጣት እና ረጅ ተቋማት ትብብራቸውን ማጠናከር አንዲችሉ በጋራ መሠራት አንዳለበት ማሳሰብ እወዳለሁ” ብለዋል። በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ የሚሳተፉ የጤና ሳይንስ አሥተዳደር ፣የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና የማኅበረሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በአግባቡ ኀላፊነታቸውን አንዲወጡ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚኾንባቸው ወረዳዎች የተመረጡት የአካባቢው የሥራ ኀላፊዎች ባላቸው ቁርጠኝነት፣ ወረዳዎቹ ባላቸው ተጋላጭነት፣ ከዚህ በፊት በተደረጉ የጤና ሪፖርቶች እና ሌሎች ምክንያቶች ስለመኾኑ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!