“የአማራ ማንነታችን እንደጋለ ብረት ይፈተን እንደኾነ እንጅ ከቶውንም ሊሰበር አይችልም” የጠለምቱ ታሪክ አዋቂ አባት ተዘራ መሰለ

97

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለሶስት አስርት ዓመታት የአማራው ኹነኛ የማንነት ማጠንጠኛ ጥያቄ ኾነው ሲነሱ የነበሩ ቦታዎች አመክንዮ አልባ በኾነ የፖለቲካ ውሳኔ ማንነታቸውን የተነጠቁ በ1984 ዓ.ም ነበር። ይህ ሲኾን የአካባቢውን ነዋሪዎች አሳትፎ፣ ይሁንታቸውንም አረጋግጦ ሳይኾን የነዋሪዎችን ነጻነት በሚነፍግ፣ ማንነትንም በሚያጠፋ መልኩ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ።

መሬቱን በጉልበት ከመንጠቅ በዘለለ የሕዝቡን ነባር ማንነት በአዲስ ማንነት ለመተካት በርካታ አሻጥሮች ተሰርተዋል። “እምቢ ለማንነቴ” ያሉት ደግሞ በርካቶች በግፍ እንዲጠፉ ተደርገዋል። ይህ እየኾነም የማንነት ጥያቄዎች ጎልተው ያልተሰሙበት ጊዜ አልነበረም። የግፉ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ፤ ሕዝባዊ ማዕበል እየገፋ መጣና የለውጥ ብርሃን መታየት ጀመረ። ከማይነጥፈው የተከዜ ወንዝ መለስ ሙሉ ጠለምት ለዓመታት የታገለለትን ነጻነት አገኘ።

አቶ ተዘራ መሰለ ስለ ማይጠብሪ እና አካባቢው ጠንቅቀው የሚያውቁ የ80 ዓመት የታሪክ ዋርካ ናቸው። ታሪክ አዋቂው “ማይጠብሪ ተወልጀ ያደግሁበት እና ክፉ ደጉን እያየሁ ያረጀሁበት ነው” ይላሉ። ተወልጀ ያደግኩባት የአማራ ጥንተ ርስት የኾነችው ማይጠብሪ በግድ የተጫነ አዲስ ማንነት ተሰጥቶን እንድንኖር ተገደን ነበር ይላሉ ። ታሪክ አዋቂው የአካባቢው ነዋሪዎች የአማራ ማንነታቸው እንዲቀየር መንግሥታዊ አሠራር ተቀርጾ ዘመቻ ይደረግ እንደነበር መስክረዋል። ማንነት እና ነጻነታቸውን ለማስከበር የተንቀሳቀሱ በርካታ የአካባቢው ተወላጆችም ስውር የጥፋት በትር አርፎባቸዋል፣ በአደባባይም ተረሽነዋል። የነሱ የኾነውን ሁሉ በጉልበት ተነጥቀዋል ይላሉ።

የማይጠብሪው አባት “ከተከዜ ወዲ ማዶ ፣ በጠለምት ምድር አማራዊ ማንነት እንደጋለ ብረት ይፈተን እንደኾነ እንጅ ከቶውንም ሊሰበር አይችልም” ሲሉ ይናገራሉ። አማራ ግብሩም፣ ድንበሩም ይታወቃል፤ የሰው አይነካም የራሱን አያስነካም። አማራ በደጁ የመጣን እንግዳ አልማጅ፣ እሱም በሄደበት ሁሉ ከወገኑ በፍቅር ለማጅ መኾኑን ዕድሜ ጠገቡ አባት የኖሩበትን እውነት ተናግረዋል።

ባለፋት 30 ዓመታት ዜጎችን ምስቅልቅል ውስጥ አስገብቶ ሥለቆየው የማንነት እና የወሰን ጉዳይ በእድሜያቸው የሚያውቁትን እንዲያጋሩኝ ጥያቄ አቀረብኩላቸው። እንደማሳያ የማይጠብሪን አካባቢ አነሳሁ። ብዙ ማብራሪያ አልሰጡኝም። ትንፋሻቸውን ዋጥ አድርገው ሁለት አረፍተ ነገር ተነፈሱ። አንደኛው አረፍተ ነገራቸው “የማይጠብሪን የአማራ ማንነት መመስከር – ወተት ነጭ ነው ብሎ እንደማስረዳት ይቆጠራል” አሉኝ። የወተትን ነጭነት ሁሉም አውቆት ያደረ የማያሻማ ሀቅ ነው፤ ማይጠብሪ የወተትን ንጣት በሚስተካከል እውነት አማራዊ ማንነት አላት ሲሉ ይናገራሉ።

ሁለተኛው አረፍተ ነገራቸው ደግሞ ስለወሰን ጉዳይ የጠየቅኋቸውን የመለሱበት ነበር። “አፍ አልባው ህያው ምስክር፣ የማይነጥፈው ተከዜ ምናለ እሱ ቢናገር” አሉኝ። እንደ እድሜያቸው የረዘመ ብዙ መረጃና ማስረጃ ቢኖራቸውም ታውቆ ያደረን ሀቅ ደጋግሞ መናገር ፉይዳ የለውምና ጉንጫቸውን ማልፋት አልፈለጉም።

“ይልቁንስ መልሰን ያገኘነውን ትክክለኛ ማንነት እና አንጻራዊ ነጻነት በውል አጥብቀን በመያዝ በሙሉ ልብ ወደ ልማት እንግባ” ሲሉም ቀጠሉ። አቶ ተዘራ አሁን ላይ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት አሰፈላጊውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ተዘራ በመንግሥት ቁርጠኝነት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አድንቀዋል። ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም ስለሌለ ሰላም ለሚፈልግ ሁሉ ሰላም መስጠት አስፈላጊ ነው ሲሉም ገልጸዋል። የአካባቢው ወጣቶች ታሪካቸውን እና ማንነታቸውን ጠንቅቀው በማወቅ ይህንን ሊያጥፍ የሚችል ማንኛውንም አካል በጋራ እምቢ ማለት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል። የሕዝቡ ማንነት ተከብሮ በሰላም ይኖር ዘንድ መንግሥት ሳይውል ሳያድር አስፈላጊውን ሁሉ ሕጋዊ እውቅና እንዲሰጥም የዕድሜ ባለጸጋው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ተዘራ በጦርነት የወደሙ የአከባቢው መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ሥራ የበለጠ እንዲጠናከር እና ተቋማት በሙሉ አቅም ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ መንግሥት እና መላ ኢትዮጵያዊያን መረባረብ እንዳለባቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማዳበሪያ ስርጭቱ ለሕገ ወጥ ነጋዴዎች የስርቆት በር ከፍቷል ” አንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አርሶ አደሮች
Next articleየኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን የተሻለ እና ጠንካራ ለማድረግ የረጅ ድርጅቶች እና ሀገራዊ ተቋማት ትብብር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።