ኢንስቲትዩቱ ሦስት ሚሊዮን ሀገር በቀል እጽዋትን ለተከላ አዘጋጅቷል።

71

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአየር ንብረት ለውጥን የተላመዱ ሦስት ሚሊዮን የሀገር በቀል ዕጽዋት ችግኞች ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዎ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚውሉ ሦስት ሚሊዮን የሀገር በቀል ዕጽዋት ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ተቋሙ የሀገር በቀል እጽዋትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ እጽዋቶቹ ለብዙ ሺህ ዓመታት በሀገሪቱ የቆዩ ስለሆኑ የአየር ንብረት መለዋወጥን የተለማመዱ ናቸው ብለዋል።

ለችግኝ ተከላ ከተዘጋጁ የሀገር በቀል ዕጽዋቶች መካከል የኮሶ ዛፍ፣ ዝግባ፣ ዋርካ፣ ወይራ፣ ጽድ እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ለመድኃኒትነት፣ ለከብት መኖ፣ አበባቸው ለንብ ምግብነት የሚውል፣ ብልን የሚቋቋሙና ለባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት የሚያገለግሉ የሀገር በቀል ዕጽዋቶች እየለሙ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገር በቀል ችግኞቹ የሚዘጋጁት በስፋት በጅማ፣ በሻሸመኔ፣ በሐረር፣ በባሌ ጎባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ማዕከላት መሆኑን አስታውቀዋል። ዶክተር መለሰ እንደተናገሩት፤ የሀገር በቀል ዕጽዋቶቹ ለመብቀል ብዙ ውኃ የማይወስዱና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚረዱ መሆናቸውን ጥናቶች ያመላክታሉ።

ባሕር ዛፍን ጨምሮ ከውጪ ሀገራት የመጡ አብዛኛዎቹ ዕጽዋቶች የከርሰ ምድር ውኃን አሟጦ የመጠቀም አቅማቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ዶክተር መለሰ፤ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ተክሎች ሳይንሱ እንደሚያሳየው ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መንስኤ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።

ከጥቅሙ አንጻር አርሶ አደሮችና ተቋማት ሀገር በቀል ዕጽዋትን በስፋት እንዲጠቀሙ የማበረታታት ሥራ ይከናወናል ብለዋል። ሀገር በቀል ዕጽዋቶቹ ለትምህርት ቤቶች፣ ለክፍለ ከተማዎች፣ ለመንግሥት ተቋማትና ለአርሶ አደሮች እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የተመናመኑ አካባቢዎችን በመለየት እና የአየር ሁኔታውን በማጥናት የትኛው ተክል ለየትኛው አካባቢ ይስማማል የሚለውን በመለየት እየሰራ ይገኛል። በአየር ንብረት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ስነምህዳሩ እንዲያገግሙ ለማድረግ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሀገር በቀል ዕጽዋቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንዲከናወን ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት ለሀገር በቀል ዕጽዋቶች ትኩረት መሰጠቱ አበረታች ነው ብለዋል። ዶክተር መለሰ እንዳመለከቱት፤ ከዚህ በፊት በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተው የሚሰራጩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቁጥሩ ወደ 3 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቻይናው ማዕድን (ሻንዢ) ኢነርጂ ግሩፕ በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።
Next articleየደሴ ከተማ የአስፓልት ፕላንት ማምረቻ ማሽን ግዥ ተፈጽሞ ወደ ከተማዋ መግባቱን ከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።