
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አርሶ አደሮች የ2015/16 የመኸር ወቅት የእርሻ ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ይሁን እንጅ የማዳበሪያ ችግር አሳስቦናል ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ ማዳበሪያ በነጋዴዎች እጅ በስፋት ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የማዳበሪያ ስርጭቱ ለሕገ ወጥ ነጋዴዎች የስርቆት በር ከፍቷል ያሉት አርሶ አደሮቹ ነጋዴዎቹ ከአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ ብር ጭማሪ በማድረጋቸው አርሶ አደሮችን እየበዘበዙ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋንታሁን አስቻለው የግብዓት አቅርቦት እጥረት በመኸር የእርሻ ዝግጅት ሥራ ላይ ተግዳሮት እንደኾነባቸው ተናግረዋል::
ለምርት ዘመኑ 16 ሺህ ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ለማቅረብ ቢታቀድም ለወረዳው የተፈቀደው 3 ሺህ 75 ኩንታል ብቻ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጅ ካለፈው ዓመት መነሻ እጥረቱ ሊያጋጥም እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ 2 መቶ 35 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ተችሏል ያሉት ኀላፊው የቀረበውን የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በፍትሐዊነት በማሰራጨትና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ችግሩን ለመሻገር ይሰራል ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘው አርሶ አደሮቹ ከስርጭት ጋር ተያይዞ የሚያነሱት ቅሬታ የተፈጠረው ጽሕፈት ቤታቸው እንደ ማሽላ ያሉ ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎችን ለሚዘሩ ቅድሚያ በመሰጠቱና ሀምሌ ወር ለሚዘሩ በአጭር ጊዜ ለሚደርሱ ሰብሎች በቀጣይ የዘር ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መልኩ ይሰራጫል በመባሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከሕገ ወጥ ነጋዴዎች ጋር በተያያዘ እንደተባለው ችግሩ አለ ያሉት ኃላፊው ሕገ ወጥ ነጋዴዎቹ ለወረዳው የመጣውን ሳይሆን ከሌሎች አከባቢዎች በሕገ ወጥ መንገድ በማምጣት እየሸጡ መሆኑን ስለማረጋገጣቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ ማዳበሪያው ከወረዳው የወጣ ባይሆንም እንቅስቃሴው ሕገ ወጥ በመሆኑ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
የመጡ ማዳበሪያዎችን በቀጥታ ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችንም የመቆጣጠር ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በወረዳው በ2015/16 የመኸር ወቅት 7 ሺህ 664 ሄክታር መሬትን በሰብል ለመሸፈንና 192 ሺህ 243 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ:- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!