የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባሕል መድኃኒቶችን በሳይንሳዊ መንገድ እያዘጋጀ ነው።

125

👉ሦስት መድኃኒቶች በቅርቡ ሙከራ ይደረግባቸዋል።

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባሕል መድኃኒቶችን በሳይንሳዊ መንገድ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተያዘው ዓመት በሳይንሳዊ መንገድ የተቀመሙ ሦስት የባሕል መድኃኒቶች በሰዎች ላይ ይሞከራሉ ተብሏል፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በደብረ ብርሃን በተለይ አንኮበር በሚባለው አካባቢ ከቦታው ታሪካዊነት እና ከመሬቱ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ሊባል በሚችል መልኩ ለመድኃኒት ቅመማ የሚውሉ ዕፅዋት የሚገኙበት ሥፍራ ነው።

እነዚህን ዕፅዋቶች በመጠቀም የድሮ አባቶች መድኃኒት ይቀምሙ እንደነበር የጠቀሱት ዶክተር ንጉስ፤ የጥንት የአንኮበር ቤተ መንግሥት በዚያ አካባቢ በመሆኑ ምክንያት እና በጊዜው ሳይንሳዊ መድኃኒቶች እንደልብ የማይገኙ በመሆኑ ለባሕላዊ ሕክምና የሚውሉ ዕፅዋት በአካባቢው ሆን ተብሎ እንዲራቡ መደረጉን ጠቁመዋል።

የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሲታመሙ ሕክምና የሚያገኙት ከዚሁ ሥፍራ እንደነበር አስታውሰው፤ አካባቢው ከፍተኛ መሆኑና በአብዛኛው ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ማግኘቱ ዕፅዋቱ እስካሁን እንዲቆዩ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የዕፅዋቱን ቅመማ እና መድኃኒትነት የሚያውቁ ረጅም ዕድሜ ያላቸው አባቶች እና እናቶች አሁንም በአካባቢው መኖራቸውን እንደ ዕድል በመጠቀም ዩኒቨርሲቲው አብሮ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እነዚህ አባቶች እና እናቶች ለማመን የሚከብዱ በሽታዎችን ቅጠል በጥሰው ማዳን የሚችሉ መሆናቸውን ነው ዶክተር ንጉስ የገለጹት።

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይህንን በመገንዘብ ሀገር በቀል የሆነውን የአባቶችን ዕውቀት ወደ ዘመናዊ ዕውቀት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አባቶች እና እናቶች እስካሁን እየተጠቀሙበት ያለውን የዕፅዋት የመድኃኒት ቅመማ ዩኒቨርሲቲው ፈትሾ አብዛኞቹ ቅመማዎች ውጤታማ ሆነው መገኘታቸውን አስረድተዋል።

የባሕላዊ መድኃኒቶችን የአቀማመም ሥልት በማጥናት ሳይንስ በሚቀበለው መልኩ ለማድረግ የተለያዩ ምርምሮች እየተሠሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሥራው እየተሠራ የሚገኘውም የመድኃኒት ቅመማ ዕውቀቱ ካላቸው አባቶች ጋር በመሆን ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በርካታ መድኃኒቶች በቅመማ እና በሙከራ ደረጃ እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአይጦች እና በሌሎች ከሰው ጋር ተመሳሳይ የሰውነት ሥርዓት ባላቸው እንስሳት ላይ ሙከራቸው ተጠናቆ በሰው ላይ ሊሞከሩ የተዘጋጁ ሦስት መድኃኒቶች በያዝነው ዓመት ሙከራቸው ይጠናቀቃል ብለዋል።

መድኃኒቶቹ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሙከራ ደረጃዎችን ሲያጠናቅቁ ወደ ምርት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

የመድኃኒት መቀመሚያ ዕፅዋቱ እንዳይጠፉ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ የዕፅዋት ማዕከል እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ለዕፅዋት ማዕከሉ 36 ሄክታር መሬት ርክክብ ተካሂዶ ለመጀመሪያ ዙር በ14 ሄክታር ላይ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን
Next articleየቻይናው ማዕድን (ሻንዢ) ኢነርጂ ግሩፕ በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።