“አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን

100

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በጋምቤላ ክልል ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በማስመልከት በጋምቤላ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በዓዋጅ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘጋጀት፤ጥናትና ምርምሮችን በማከናወንና ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ረገድ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ሀሳቦችን ከሕዝቡ ለማሰባሰብ በያዘው እቅድ መሰረት ከነገ ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምክክር ሂደት ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ይጀምራል ብለዋል።

በክልሉ በዚሁ በሚጀመረው የልየታና አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በወረዳ ደረጃ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ዘጠኝ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።

ከተለዩት አደረጃጀቶች መካከል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ፣እድሮች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ የነዚህን የተሳታፊ ልየታ ተግባራት ለማከናወን በተባባሪነት ለሚሰሩ አካላት በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንደሚገባም ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በተሳታፊ ልየታው በክልሉ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና ሌሎችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ሥራዎች መቃናት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል” ዶክተር ጋሻው አወቀ
Next articleየደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባሕል መድኃኒቶችን በሳይንሳዊ መንገድ እያዘጋጀ ነው።