
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ከሰሞኑ ባካሄደው ስብሰባ እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ የሥልጠና መድረክ ተጀምሯል፡፡ ከሰኔ 05/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚቆየው ድርጅታዊ ሥልጠና የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ የሥራ ኀላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ሀገራዊ መልካም አፈጻጸሞች የመኖራቸውን ያክል ፈታኝ ችግሮችም አጋጥመውናል ብለዋል የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር)። የተገኙ ድሎችን ለማስፋት እና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት መሠል ድርጅታዊ ሥልጠናዎች ያስፈልጋሉም ብለዋል፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተካሂዶ አበረታች ለውጦች ተገኝተውበታል ያሉት ዶክተር ጋሻው ከዚህ ሥልጠናዊ መድረክ የሚጠበቁ ብዙ የጋራ አመለካከቶች አሉ ብለዋል፡፡
ዶክተር ጋሻው እንዳሉት አሁን ያለንበት ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ኹኔታ ተለዋዋጭ የፖለቲካ አዝማሚያዎች የሚስተዋሉበት ነው። እነኝህን ነባራዊ ሁኔታዎች በአግባቡ ተረድቶ የሚመራ ፖለቲካዊ መሪ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ከሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ በክልል ደረጃ ለሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ሥልጠናዊ መድረክ መዘጋጀቱ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ትውልዱ ትናንት ላይ ኾነው ዛሬን የማየት ልዩ ተሰጥኦ የነበራቸው አባቶቹ ቀንበር ተሸካሚ ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው፤ ፈተናዎችን በብስለት እና በትዕግስት እያለፉ ሀገር ማስቀጠል ከትናንት የተወረሰ ትምህርት ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ነጋዴዎች የሚፈጥሯቸውን ፈተናዎች እና ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሕብረ ብሔራዊ የፖለቲካ አሰላለፍ እና ተሻጋሪ ትግል ስለሚያስፈልግ አመራሩ ራሱን ከነባራዊ ሁኔታዎች አንጻ ማየት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በዘለቀ ትግል እና ፈተና ውስጥ ከሌሎች ወንድም እና እህቶቹ ጋር በመኾን ሀገር ያጸና ሕዝብ ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው በፈተናዎች ያለመውደቅ ምክንያቱም ለዘመናት ያነበረው ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሀገር በቀል የእርቀ ሰላም እሴቱ ጠንካራ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ጋሻው ክልሉ ባለፉት ጊዜያት የሀገሪቱን እና የክልሉን ኅልውና የሚፈታተኑ ችግሮች ገጥመውት እንደነበር አንስተው በምክክር፣ በሽምግልና እና በእርቀ ሰላም በርካቶቹ ችግሮች ተፈትተዋል ብለዋል፡፡ ልዩነቶችን በሽምግልና እና በእርቀ ሰላም የመፍታቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በብዝሃነት የሚያምን እና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ ሥለመኾኑ ያነሱት ዶክተር ጋሻው፤ ይህንን ነባር እሴት ለመበረዝ የሚሞክሩ ዋልታ ረገጥ ሃሳቦች ነበሩም ብለዋል፡፡ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ስሌት ዘመን ያለፈበት አካሄድ በመሆኑ አዳዲስ ሃሳቦችን ማየት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ሥራ በትኩረት እንደሚመራ አንስተዋል፡፡
መድረኩን የሚመሩት እና የሚያስተባብሩት የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው ያሉት ዶክተር ጋሻው፤ ብልጽግና ኅብረ ብሔራዊነቱን መሠረት ለማስያዝም የክልል ከፍተኛ መሪዎች ወደ ተለያየ ክልሎች እየሄዱ መድረኩን ይመራሉ ብለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ወንድማማችነትን ከማጠናከሩም በላይ አንዱ ሌላውን የሚረዳበት አውድ ስለሚፈጥር ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለዚህ መሰል አካሄድ እንግዳ እንዳልኾነ በማንሳት “የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!