ከክረምት መግባት ጋር በተያያዘ በተመላሽ ተፈናቃይ ዜጎች አካባቢ ወባና መሰል በሽታዎች እንዳይከሰቱ ክትትል እየተደረገ መኾኑ ተገለጸ፡፡

163

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ ወደ ቀያቸው ከተመለሱት መካከል በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአበርገሌና ጻግብጅ ወረዳ ተፈናቃዮች ይገኙበታል፡፡ የክረምቱን መግባት ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን ወረርሽኝ ለመከላከል እየሠራ መኹኑን የአበርገሌ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኀላፊ ወንድሙ ደመቀ ከዚህ በፊት በወረዳው የአባ ሰንጋና ኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር አንስተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን ነው የተናገሩት፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የአጎበር ሥርጭት እና የቤት ለቤት ቅድመ ምርመራና ሕክምና ሥራ እየተሠራ ቢኾንም የመመርመሪያ ኪትና የመድኃኒት እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡

ኀላፊው እንዳሉት ከመደበኛ መድኃት አቅርቦት ባለፈ ለድንገተኛ የመድኃኒት ግዥ ተጠይቆ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በኬሚካል እጥረት ምክንያት የወባ መድኃኒት ርጭት አለመደረጉንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይ ሊከሰት የሚችለውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል ወረዳው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የግብዓት እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ የባለሙያዎች የአቅም ማጎልበት ሥራም እንደሚያስፈልግ ነው ኀላፊው ያነሱት፡፡

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማስተባበሪያ ማእከል ተወካይ ሥራ አሥኪያጅ አሞኘ በላይ እንዳሉት ተፈናቅለው በተመለሱ አካባቢዎች ወረርሽኝ እንዳይከሰትና ከተከሰተም ቀድሞ ምላሽ ለመስጠት ባለሙያ መድቦ የቅኝትና አሰሳ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ወባን ለመከላከል አጎበር ተሠራጭቷል፤ አሁን ላይም የወባ መድኃኒት ለማሠራጨት በዝግጅት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ እጥረት ያጋጠሙ መድኃኒቶች እንዲሟሉ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡንም አስረድተዋል፡፡

ከንጽህና እና ከንጹህ ውኃ አቅርቦት ጋር ሊከሰት የሚችልን ወረርሽኝ ለመከላከልም ክትትል እየተደረገ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ማኅበረሰቡም የወባና የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መሥራት እና አጎበርን በተገቢው መንገድ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ውኃን አፍልቶና አክሞ መጠቀም እና የምግብን ንጽህና በመጠበቅ ራስን ከበሽታ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡ የበሽታ ምልክት ከታየ ደግሞ ፈጥኖ ለጤና ባለሙያዎች ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ክልል ካሳለፈው ውስብስብ ፖለቲካዊ ፈተና አንጻር ሥልጠናው አስፈላጊ ነው” አቶ እርስቱ ይርዳው
Next article“የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል” ዶክተር ጋሻው አወቀ