በቻይና በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተከታትለው በመግባት አሸነፉ

138

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቻይና የላንዡ ከተማ በተካሄደ የወንዶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም አገራት በተደረጉ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።

ከእነዚህ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል በ2023 የላንዡ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ በበላይነት ጨርሰዋል።

በተለይ በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

በውድድሩ አትሌት ሃይለማርያም ኪሮስ በአንደኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን አፈወርቅ መስፍን፣ ሃይማኖት አለው፣ ሃይሌ ለሚ፣ አባይነህ ደጉ፣ ዮሐንስ መካሻ፣ ዱበር አብዲሻ እንደየቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶች ደግሞ አትሌት ለተብርሃን ሃይላይ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ አትሌት ታደለች በቀለ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች።

በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ የማራቶን ውድድር የተካሄደ ሲሆን በሴቶች አትሌት ዝናሽ ደበበ በአንደኝነት አጠናቃለች።

በኔዘርላንድ በተካሄደ ግማሽ ማራቶን ውድድር ንግስቲ ሃፍቱ በአንደኝነት ጨርሳለች።

በዚህ ውድድር በወንዶቹ አትሌት ሃፍቱ ተክሉና አሸናፊ ኪሮስ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።

በአሜሪካ ኒዮርክ በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የቦታውን ሰዓት በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች።

በፈረንሳይ በተካሄደ 5 ሺህ ሜትር ውድድር ደግሞ አትሌት መዲና ኢሳ የቦታውን ክብረ ወሰን ሰዓት በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለፉት አራት ዓመታት ተኩል በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በተካሄዱ ተግባራት ለውጥ መመዝገቡን የፍትሕ ፕሮጀክት ገለጸ።
Next article“የአማራ ክልል ካሳለፈው ውስብስብ ፖለቲካዊ ፈተና አንጻር ሥልጠናው አስፈላጊ ነው” አቶ እርስቱ ይርዳው