ለፉት አራት ዓመታት ተኩል በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በተካሄዱ ተግባራት ለውጥ መመዝገቡን የፍትሕ ፕሮጀክት ገለጸ።

81

አዲስ አበባ: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአሜሪካን ኢምባሲ አማካኝነት በዩ.ኤስ.ኤይድ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ከአራት ዓመት በላይ ሲሠራ የቆየው ፍትሕ ፕሮጀክት የማጠቃለያ ፕሮግራሙን በሸራተን አካሂዷል።

የአሜሪካ ኢምባሲ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ላለፋት አራት ዓመት ተኩል ፍትሕ የተሰኘ ፕሮጀክት አቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል።

ፕሮጀክቱ የሚሠራቸውን ሥራዎች ለመደገፍም ዩ.ኤስ.ኤይድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲኾን ፕሮጀክቱ በቆይታው ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የማጠቃለያ ፕሮግራም በሸራተን አካሂዷል ።

በተለይም ለአማራና ኦሮሚያ ክልል ዳኞች የአቅም ግንባታ እና የልምድ ልውውጥ ተግባራትን ማከናወኑንና በፍትሕ አሰጣጡ ላይ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን የፕሮጀክቱ ኀላፊ ዴቪድ ዲ ጀልስ ገልጸዋል።

የዩ.ኤስ.ኤይድ ምክትል ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ቶም ስታል ዩ.ኤስ.ኤይድ.ፍትሕ ፕሮጀክት የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ ይኾኑ ዘንድ የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። በሥራውም ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል። ወደፊትም የተሻለ የፍትሕ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

ፍትሕ ፕሮጀክት በቆይታው በአማራ ክልል ለ282 ዳኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሥጠቱን፣ በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ በሬዲዮና ቴሌቪዥን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራቱንና የፀጥታ ተቋማትን ተግባራት ዲጅታላይዝ በማድረግ በኩልም ድጋፍ ማድረጉ በመድረኩ በፍትሕ ሚኒስቴር ተገልጿል ።

የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ኾነው ሥራቸውን ማከናወን ከቻሉ የፍትሕ ሥርዓቱ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወኑ ተብራርቷል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰቱ አፋጣኝ እና ገለልተኛ መልስ መሥጠት የሚያስችለውን ልምድ ማካፈል መቻሉን ተገልጿል። ከፍትሕ ተቋማት ጋር መሥራት መቻሉ ተቋሙ የተጣለበትን ኀላፊነት እንዲወጣ አግዞታልም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ሕጎችን ለማሻሻል፣ ጥራት ያለውና ገለልተኛ ፍርድ እንዴት መሥጠት እንደሚቻል፣ የዳኝነት ነፃነት እንዲጎለብት አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልጿል።

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የአማራ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል የክልል አቀፍና የሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን የተመለከተ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleበቻይና በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተከታትለው በመግባት አሸነፉ