የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል የክልል አቀፍና የሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን የተመለከተ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

339

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል የክልል አቀፍና የሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን በተመለከተ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደረጀ አማረ በዞኑ 44 ሺህ 676 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በ718 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 18 ሺህ 309 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በ62 ትምህርት ቤቶች በዘንድሮው ዓመት እንደሚፈተኑ ገልጸዋል፡፡ የመድረኩ ዋና ዓላማም የፈተና አሰጣጡን በተናበበ መልኩ ለማካሄድ እንደኾነ ኀላፊው ተናግረዋል።

አቶ ደረጀ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ አስታውሰው ካምናው ተሞክሮ በመነሳት የዘንድሮውን በተሻለ መልኩ ለማስኬድ ቅድመ ሁኔታዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፀጥታና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ባለድርሻ አካላት የዘንድሮውን ፈተና ካምናው በተሻለ መልኩ ለማስኬድ በፀጥታውና በትራንስፖርት ዘርፉ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠሩ ስለመኾኑ አስረድተዋል።

በዘንድሮው ዓመት የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዞኑ ሰኔ 27 እና 28/2015 ዓ.ም የሚሰጥ ሲኾን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ 30/2015 ዓ.ም ይሰጣል።

ዘጋቢ፡- ሀበሻ አንለይ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም እና መገንባት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
Next articleለፉት አራት ዓመታት ተኩል በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በተካሄዱ ተግባራት ለውጥ መመዝገቡን የፍትሕ ፕሮጀክት ገለጸ።