በሕዝቡ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት እና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ጥረት አብረው እንደሚሰሩ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ አማራዎች አረጋገጡ፡፡

193

በሕዝቡ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት እና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ጥረት አብረው እንደሚሰሩ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ አማራዎች አረጋገጡ፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ከሚኖሩ አማራዎች እና የአማራ ጉዳይ ይመለከተናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በሜሪላንድ – ሲሊቨር ስፕሪንግ ዛሬ ተወያይተዋል፡፡

“የአማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት ነው ውይይቱ የተካሄደው። ውይይቱን የመሩት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡

በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት፣ ልማት እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው ምክክር ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ላይ የሚደርሰው በደል እንዲቆም መሥራት እንደሚገባ እና አማራውን እረፍት የሚነሱትን አካላት ማስቆም ትኩረት እንዲሰጠው ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚመጡ ባለሀብቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ክልሉን ለማልማት ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ እና ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ከሚሰሩ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት በማጠናከር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ማሳደግ ትኩረት እንዲሰጠው፤ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ስለሚመለሱበት መንገድም ግልጽ መፍትሔ በማስቀመጥ እንዲሰራበት ነው የጠየቁት፡፡

ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ አማራዎች ኅልውና ጉዳይ በትኩረት እንዲሰራበት የጠየቁት ተወያዮቹ ለዘር ተኮር ፖለቲካ በር ከፋች የሆነው ህገ መንግስቱ እና ዘር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀቶች መፍትሔ ካልተሰጣቸው በሕዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ለማስቆም አስቸጋሪ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ አረም ማስወገድ፣ በዙሪያው ወደ ሐይቁ የሚገቡ በካይ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ማስቆም እና ብዝሀ ሕይወቱን ከጥፋት መታደግ ትኩረት እንዲሰጠውም ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ በውሕደቱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዴት ሊመለሱ እንደታሰበም ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

የሥራ ኃላፊዎቹም አዴፓ እና የክልሉ መንግሥት ለሕዝቡ ተጠቃሚነት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ፣ ጥረቱን ደግሞ ሁሉም በየሚመለከተው ዘርፍ በተግባር እንዲደግፍ ለተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ ጉድለቶችን በምክክር በማሻሻል፣ ጥንካሬዎችን ደግሞ በማጎልበት የተሻለ ሥራ ለመሥራት በውጭ የሚኖሩት አማራዎች እንዲተባበሩም ነው ጥሪ ያቀረቡላቸው፡፡

የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግም አማራ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ፣ ሕዝቡንም እንዲጠቅሙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ ስለውሕድ ፓርቲው ጉዳይ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ እንደተሰራበት፣ በዚህም የአማራው እና የሌሎችም ሕዝቦች ጥያቄዎች ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደሚፈቱ በግልጽ እንደተመላከተ አቶ ዮሐንስ አስገንዝበዋል፡፡

ተወያዮቹ በክልሉ ሕዝብ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት እና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት እና አዴፓ በሚያደርጉት ጥረት አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፤ አልማን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ – ከሜሪላንድ – ሲሊቨር ስፕሪንግ

Previous articleአርሰናል ኡናይ ኢሚሬይን አሰናበተ፡፡
Next articleበውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።