
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም እና መገንባት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የምክክር መድረኩ ዓላማ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሔደው ጦርነት ሳቢያ የደረሰውን ጉዳትና መልሶ ማቋቋም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ምክክር በማድረግ ሰው ተኮር ልማት ለማጠናከርና ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማደስ እንደሆነ ተገልጿል።
የደረሰውን ጉዳትና መልሶ ማቋቋም ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት በሸፈናቸው ክልሎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውድመት መድረሱን ነው የተጠቆመው።
በማኅበራዊ፣ በምርት፣ በመሰረተ ልማት፣ እና ባለብዙ ዘርፎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጾ፤ ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም ጥረት እንደሚያስፈልግ ነው የተጠቆመው።
የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ባንክ እና የልማት አጋሮች የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝ ግጭቱ ያደረሰውን ውድመትና ጥፋት እንዲሁም የፈጠረውን ፍላጎት አካታች መረጃ ለመስጠት የጉዳት ፍላጎት ግምገማ ማድረኩም መካሄዱ ተመላክቷል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በምክክር መድረኩ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ሚኒስትሮች፣ በኢትዮጵያ የአገራት አምባሳደሮች፣ የልማት አጋሮች፣ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!