“ስታዲዬሙ ውድድሮችን ለማስተናገድ በካፍ የተጠየቀውን መስፈርት ማሟላቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና የካፍ ተወካዮች በቦታው ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡” የወልድያ ከተማ አስተዳድር

147

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) 105 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 26 ባለሀብቶች በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ ግንባታ ላይ እንደሚገኙም ተገልጧል። ከ250 ሚለዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በአገልግሎት ዘርፍ ፈቃድ መውሰዳቸውን የወልድያ ከተማ አስተዳድር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የፕሮጀክቶች ክትትል እና ድጋፍ ኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ አራጋው ተገኘ እንደገለጹት ባለፋት ዓመታት በወልድያ ከተማ አስተዳድር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 191 ባለሀብቶች በባለኮከብ ሆቴል፣ በሞቴልና በሁለገብ ገበያ ማዕከል ግንባታ እና በሆቴል ደረጃ ማሻሻል ሥራ ፈቃድ አግኝተዋል።

‹‹ዘርፉ ከ30 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል›› ብለዋል አቶ አራጋው፡፡ አብዛኞቹ ባለሀብቶች በተለያዩ የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ተሰርተው ሲጠናቀቁ በወልዲያ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚደረጉ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ማረፊያ ችግር መቅረፍ እንደሚችሉ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ውል ከወሰዱት 26 ባለሀብቶች አብዛኞቹ በባለኮኮብ ሆቴሎች፣ በሎጅ፣ በሞቴል ግንባታ ላይ እንደተሰማሩ ነው ባለሙያው የተናሩት፡፡

የወልዲያ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ሙሃመድ ያሲን እንደገለጹት ደግሞ ስታዲየሙ ውድድሮችን ለማስተናገድ በካፍ የተጠየቀውን መስፈርት ማሟላቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የካፍ ተወካዮች በቦታው ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሆቴል ግንባታ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ አጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሆቴል ግንባታ ዘርፍ ውል ወስደው ሥራ ያልጀመሩ 47 ባለሀብቶች ላይም የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡ አብዛኞቹ ባለሀብቶችም ወደ ግንባታ መግባታቸውን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቶች ባወጡት ዲዛይን እና የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የማይገነቡ ከሆነ የወሰዱትን ቦታ ሊያለማ ለሚችል ባለሀብት እንደሚተላለፍ ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡

‹‹ወደ መሬት ባንክ የገቡ፣ በጨረታ የተላለፉ እና በምደባ ቢሰጡ ለተሻለ ልማት እና ለስታዲየሙ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ ሆቴሎች መስሪያ ቦታ ጨረታ ለማውጣት ቦታዎች ተለይተዋል›› ብለዋል፡፡ አቶ ሙሀመድ እንደገለጹት ስታዲዬሙን በካፍ ለማስመዝገብ በከተማው እና በዙሪያው በቅርብ ርቀት በትንሹ ሦስት የእንግዳ ማረፊያ መኖር እንዳለበት እንደ መስፈርት ተቀምጧል:: በዚህ መሠረት በከተማው አራት የእንግዳ ማረፊያዎች መስፈርቱን የጠበቁ እና የሚመጡ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የካፍ ተወካዮች በቦታው ተገኝተው ማረጋገጣቸውንም አቶ ሙሃመድ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ፎቶ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleበውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።
Next articleየኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡