
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ዩኒየኖች በአጠቃላይ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨታቸውን የክልሉ ኀብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ኀላፊ ጌትነት አማረ እና ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ የኀብረት ሥራ ማኅበራት አመራሮች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ ሞዴል ዩኒየኖችን አሠራር ተመልክተዋል።
በአማራ ክልል 27 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ዩኒየኖች አሉ። እነዚህ ዩኒየኖች እና መሠረታዊ ማኀበራት በአጠቃላይ ወደ 9 ቢሊዮን ብር እንደሚያንቀሳቅሱ አቶ ጌትነት ተናግረዋል። ዩኒየኖቹ የገጠሩን ማኅበረሰብ የቁጠባ ባሕል ማሳደግ መቻላቸውም ተገልጿል። እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ በተያዘው ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ቁጠባ በዩኒየኖች በኩል መሰብሰብ ተችሏል።
በአማራ ክልል የሚገኙ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ዩኒየኖች የብድር አገልግሎት በመሥጠት በኩል በቁርጠኝነት እየሠሩ ይገኛሉ ተብሏል። ይህም የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት።
አቶ ጌትነት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ውስጥ የሚገኙ ሶሰር እና ኮከብ የተባሉ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ዩኒየኖች ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው ብለዋል። እነዚህ ዩኒየኖች ከአንዳንድ ባንኮች የተሻለ ብድር ሰጥተዋል ነው ያሉት። ያለምንም ቢሮክራሲ አገልግሎቱን መሥጠት በመቻላቸው ማኅበረሰቡ ወደ ዩኒየኖች በመቅረብ የቁጠባ እና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እየኾነ ነው ብለዋል።
የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ዩኒየኖች በፋይናንስ ግንባታው ዘርፍ የሚጫወቱትን ሚና በመገንዘብ መደገፍ እና ማጠናከር ይገባል ሲሉ አቶ ጌትነት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሶሰር ኀላፊነቱ የተወሰነ የኀብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው መሀመድ ዩኒየኑ በ660 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተመሠረተ ነው ብለዋል። ዩኒየኑ ዳንግላ እና አካባቢውን መሰረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲኾን አሁን ላይ በእንጅባራና ጃዊ አካባቢም አገልግሎት መሥጠት ጀምሯል። አጠቃላይ የካፒታል መጠኑ ወደ 113 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። የሃብት መጠኑ 800 ሚሊዮን ብር ደርሷልም ብለዋል።
አቶ አስቻለው ሶሰር የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ዩኒየን በተለይም የባንክ ተደራሽ ያልኾነውን የገጠሩን ማኅበረሰብ የፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። ዩኒየኑ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ቁጠባ የሰበሰበ ሲኾን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ብድር አሰራጭቷል። መሰረታዊ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በውስጡ በመያዝ የገጠሩን ክፍል የቁጠባ እና ብድር አገልጎሎት ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑንም ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል።
ሌላው ምልከታ የተካሄደበት ኮከብ ኀላፊነቱ የተወሰነ የኀብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ዩኒየን ነው። ዩኒየኑ የሚገኘው በግምጃ ቤት ከተማ ነው። የዩኒየኑ መነሻ ካፒታል ከ537 ሺህ ብር ሲኾን አሁን ላይ 402 ሚሊዮን ብር መድረሱን ሥራ አስኪያጁ አቶ ገበያው ውድነህ ተናግረዋል።
ዩኑየኑ አነስተኛ ደመወዝ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በተመጣጣኝ ወለድ ብድር ማቅረቡ ተመራጭ አድርጎታል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ። በተለይም በከተማ አካባቢ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ለቦታ ምሪት ካሳ የሚውል ብር በመሥጠት የቤት ባለቤት እንዲኾኑ ዩኒየኑ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዩኒየኑ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም ለመኾን ዘመናዊ ቢሮዎችን እና ቴክኖሎጅ እየተጠቀመ እንደሚገኝም አቶ ገበያው ተናግረዋል።
ጉብኝት ያደረጉ የሌሎች ዩኒየኖች ኀላፊዎች ከኮከብ እና ከሶሰር ዩኒየን ልምዶችን በመውሰድ ጠንካራ እና የማኅበረሰቡን የብድር ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። አሠራራቸውንም ከወረቀት ወደ ሶፍት ዌር በመቀየር ዘመናዊ እና ደኀንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ አገልግሎት ለመሥጠት በትኩረት እንደሚንቀሳቀሱ አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!