
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እና የሩሲያ ኢምባሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እና የሩሲያ መንግሥት ግንኙነት የሚጀመረው የዩኒቨርሲቲው ምሥረታ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው።
ቀዳማዊ ግርማዊ ኃይለ ሥላሴ ከቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት የአሁኗ ሩሲያ ጋር በመተባበር ነበር የመሠረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት። ዛሬ የተደረገው ሥምምነትም ጃንሆይ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት በፖሊ ግቢ ነው። ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲም የጃንሆይ ውጤት ነውም ይባላል።
ዛሬ የተደረገው ስምምነት በጃንሆይ ዘመን የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከር እና የበለጠ ለመሥራት ነው ተብሏል። ግንኙነቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመላክቷል።
ስምምነቱን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) እና በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ትርኪሂን ፈርመውታል። የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ( ዶ.ር) በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ ቀን አምባሳደሩ በመገኘታቸው አመስግነዋል። የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ታሪካዊና የቆዬ መኾኑንም አንስተዋል። ሩሲያ ለኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር መኾኗንም ተናግረዋል።
ስምምነቱ በኒውክለር ኢንጂነሪንግ እና በሌሎች ዘርፎች ልምድ ለመውሰድና ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ የባሕርዳር ቴክኖሎጂና ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር
ዶክተር ቢምረው ታምራት ናቸው። የተደረገው ስምምነት ለዩኒቨርሲቲው ታላቅ ጉልበት ይኾነዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ትርኪሂን የዛሬው ቀን ልዩ መኾኑን ገልጸው ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የነበረን ግንኙነት የቆዬ ነውም ብለዋል። ከዩኒቨርሲቲው ጋር ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
ሀገራቸው ከአሁን ቀደምም በልዩ ልዩ ዘርፎች አብራ ስትሠራ መቆየቷንም ገልጸዋል። ትብብሩ እየሰፋ የሚሄድ መኾኑንም አንስተዋል። ከሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ሩሲያ የነፃ የትምህርት እድልን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገች መኾኑንም ገልጸዋል።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እና ብልፅግና እመኛለሁም ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲው ገና ጎልማሳ ነው ያሉት አምባሳደሩ ወደፊት እንዲያድግ መሠራት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!