“ከሠላም የተሻለ አማራጭ የለንም” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ

1278

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ረዳ የተመራ የትግራይ ክልል ልዑክ ባሕር ዳር ይገኛል፡፡ ሁለቱ ርእሳነ መሥተዳድሮች በሁለቱ ክልል ሕዝቦች እና ቀጣይ የሠላም ጉዞ ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ከተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተገኝተው ለርእሳነ መሥተዳድሮቹ ጥያቄ ያቀረቡ የከተማዋ ነዋሪዎችም የሠላም ግንኙነቱን ዘላቂ ለማድረግ የአመራሩ ቁርጠኝነት ምን ያክል ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ከጦርነት ኪሳራ ካልሆነ ትርፍ እንደማይገኝ ቀድሞውንም ያውቃል ያሉት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ስማቸው ንጋቱ በእምነት፣ በባህል፣ በማንነት እና በድንበር አንድ የሆነን ሕዝብ መነጣጠል አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ዳርጓል ብለዋል፡፡ ከባለፈው ጥፋት ተምሮ ሥህተትን ማረም ይሻላል ያሉት አቶ ስማቸው አመራሩ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ምን ያክል ዝግጁ ነው ብለዋል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ የዝቡጥላ ካሳ 2011 ዓ.ም ሠላም እና እርቅ እንዲወርድ መቀሌ ድረስ ከተጓዘው የሠላም ልዑክ ጋር አብረው ተጉዘው እንደነበር አንስተዋል፡፡ በወቅቱ የሠላም አማራጮች መገፋታቸው ባለፉት ዓመታት ለከፈልናቸው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች ዳርገውናል ያሉት ጠያቂዋ አሁንስ የተጀመረውን የሠላም ጅማሮ ዳር ለማድረስ ምን ያክል ተዘጋጅታችኋል ብለዋል፡፡

ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ለማጥበብ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያለው ቁርጠኝነት፣ እየሄደበት ያለውን ርቀት እና ዝግጁነት ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ዋጋ የማይጠይቅ የሠላም አማራጭ ሳለ በፖለቲከኞች የጠብ ርሃብ ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል ብለዋል፡፡ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ልዩነቶቹ ከአማራ እና ትግራይ ሕዝብ በታች ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁን የጦርነትን ምዕራፍ ዘግተን የሠላም አማራጮችን የምናይበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

“የሁከት እና ግርግር አጀንዳዎች የሚታያቸው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ለሕዝብ ካሰብን እና ከሠራን ከሠላም ውጭ የተሻለ አማራጭ የለንም” ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ፡፡

ልዩነቶች ይኖራሉ ልዩነቶችን ግን በሕግ፣ በሠላም እና በመነጋገር መፍታት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ነው ያሉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ለሠላም አማራጮች ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ወደ ቀደመው ሁኔታው መመለስ አለበት፣ ትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርበታል ያሉት ዶክተር ይልቃል ተከባብረን እና ተደማምጠን ልዩነቶቻችን ለመፍታት መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ አመራሩ የጀመረውን የሠላም ግንኙነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በተለይ ደግሞ አዋሳኝ አካባቢ ያሉ የሁለቱም ክልል ሕዝቦች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዩኒቨርሲቲ እድገትና የሀገር ብልጽግና ተመጋጋቢ ናቸው” አቶ አደም ፋራህ
Next articleባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሩሲያ መንግሥት ልዩ እውቅና ሰጠ።