
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የማጠቃለያ ዝግጅት እያካሄደ ነው።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አደም ፋራህ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ለሀገርና ለዓለም ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በስኬት እንዲዘልቅ ላደረገው የባሕርዳር እና አካባቢው ማኅበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል።
የ60 ዓመት ፈተናዎችን እና ስኬቶችን በመገምገም ለቀጣይ ጉዞው መሠረት መጣሉንም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በበዓሉ አከባበር ስንቅ ማግኘቱንም ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲዎች መጠናከር ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ ከፈተኛ ነውም ብለዋል። የፖለቲካ ሥርዓቱን ለማዘመን፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እና ለሌሎች ተግባራት ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ሚና ይወስዳሉም ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲ እድገት እና የሀገር ብልጽግና ተመጋጋቢ ናቸውም ብለዋል። ሀገርም አቅሟ የፈቀደውን ያክል ለዩኒቨርሲቲዎች መስጠት ያስፈልጋታልም ነው ያሉት። ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር ግንባታ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አመላክተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች በሀገር በቀል እሴቶች ሊበለጽጉ እንደሚገባና ምርምር ሊካሄድባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የጥብብ ምንጭ እንደነበረው ሁሉ ወደፊትም ይሠራል ነው ያሉት። ቀዳሚ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመኾን እየሠራ ነውም ብለዋል። ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ለማሟላት የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም በመባል ዕውቅና ማግኘቱንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲኖር እና የኢትዮጵያ አለኝታ ለመኾን ይሠራል ነው ያሉት። በ60ኛ ዓመት አከባበር ላይ የተገኙ ልምዶችን በቀጣይም መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ለላቀ ተልእኮ እንዲዘጋጁ አደራ ብለዋል። የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጀመሩትን ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!