
የባቡር ፕሮጀክቱን የሀገሪቱ ኪሳራ ከመሆን በመታደግ የኢኮኖሚ ማሳለጫ እንዲሆን የፉክክር ምዕራፎችን መዝጋት እንደሚያስፈልግ የአዋሽ-ወልድያ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት አስታወቀ።
የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ሥራ እንዳይጀምር ያደረጉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ‹‹የባቡር ፕሮጀክቱ በኃይል እጥረት ምክንያት ሥራ አለመጀመሩን ተመልክተናል›› ብለዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የተዘለሉ የካሳ ክፍያ ቅሬታዎችንም ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት አብረዋቸው በመሆኑ ተወያይተው እንደሚፈቱ ነው የተናገሩት።
ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ችግር እንዳለበት እንደሚያነሳ የተናገሩት አቶ ተመስገን የባቡር ፕሮጀክቱ ደግሞ በሥራ ሂደት አብሮ መሥራትም ሆነ ባለቤት መሆን ያለበት መብራት ኃይል ነው በሚል መገፋፋት ሥራ አለመጀመሩን አብራርተዋል። የባቡር ፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር ያላስቻሉትን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ እንደሀገር የገቢና ወጪ ምርትን የማሳለጥ፤ ከተሜነትንና ልማትን የማፋጠን ተስፋ እንዳለው የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል። “392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዋሽ-ወልዲያ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ሥራ ያልጀመረው እንደሀገር በተፈጠረው የፋይናንስ እጥረት ነው” ብለዋል። መንግሥት ነባር ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረጉም የባቡር መስመሮቹ የተጋረጡባቸውን ችግሮች ቶሎ እንዲፈቱ ስለሚያስችል ከሁሉም አካላት ጋር በመወያየት ለትራንስፖርት ክፍት እንዲሆን እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብዱልከሪም ሙሀመድ የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር ፕሮጀክት 99 በመቶ የኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ደግሞ 70 በመቶ ደርሷል ብለዋል። የአዋሽ ኮምቦልቻው መስመር ከ6 ወር በፊት ሙከራ በማድረግ አሁን ለትራፊክ ክፍት መሆን የሚያስፈልገው ቢሆንም በኃይል አቅርቦት ችግር ሥራ መጀመር አልቻለም ብለዋል።
የባቡር ፕሮጀክቱ 40 በመቶ ሲደርስ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል የመግጠም ሥራ እንዲጀምር በተከታታይ ቢጠየቅም ሊሠራ አለመቻሉ ፕሮጀክቱን ለሁለት ከፍተኛ ችግሮች እንዲጋለጥ ማድረጉን ተናግረዋል። የተገባው ውል ሊጠናቀቅ መቃረቡ እና የምድር ባቡር ሥራ አለመጀመሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳለጥ ይልቅ ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋል ብለዋል። አቶ አብዱልከሪም የባቡር ፕሮጀክቱ እንዳይጀምር ያደረገው የኃይል አቅርቦት የፉክክር ምዕራፎች ተዘግተው በምክክር ለሀገር ኢኮኖሚ ማሳለጫ እንዲውል መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ – ከኮምቦልቻ