
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የማጠቃለያ ዝግጅት እያካሄደ ነው። ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከፍ ያለ ስም ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱና በፈጣን እድገት ላይ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ነውም ተብሏል።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባለፈ በማኅበረሰብ አገልግሎት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በ60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ለባለድርሻ እና አጋር አካላት መሥጠቱንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋማቱን ከፍ ወደላ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራም አስታውቋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) ለሀገራት እድገት የተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። በተቋም ግንባታ ደግሞ የመሪዎች ሚና አይተኬ መሆኑን ገልፀዋል። የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ አኩሪ መሪ እና የዲፕሎማሲ አውራ እንደነበሩም ገልፀዋቸዋል።
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበት ዓላማ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውን የቴክኖሎጂ ሰዎችን ለማፍራት እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ፍሬው በዘረፉ የሀገር ኩራት የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራቱንም ገልፀዋል።
ዓለማቀፋዊነት ከእሴቶቻቸው መካከል አንደኛው መሆኑንም ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው ግዙፍ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአፍሪካ ምርጥ 70ዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች አንደኛው መሆኑንም አንስተዋል።
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቹ እና ለሠራተኞቹ ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ መሥራቱንም ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲውን አረንጓዴ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የሕዝብ ተቋም መሆኑን እያረጋገጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!