
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) የከተማው የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ “የሥራ ዕድል ምንጩ መንግሥት ብቻ እንዳይሆን ለአልሚ ባለሀብቶች በራችን ክፍት ነው” ብሏል፡፡ ከጁቡቲ 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የትግራይ እና አፋር ክልሎች መዳረሻ ማዕከል ናት፡፡ ይህ መዳረሻነቷ ከገደል ስር እንዳለ ማር ከመሆኗ ውጭ እንደ ወደብነቷ ያተረፈችው አንዳች ነገር እንደሌለ የከተማዋ ኢንዱስትሪ ታሪክ ያመላክታል፡፡
የደረቅ ወደብ ጥያቄዋም ምኞት እንደሆነ ዘልቋል፡፡ መንገዶቿ በረጃጅም መኪኖች ተዘጋግተው በመጠቅጠቃቸው የተቦዳደሰው አስፓልት ውኃ ቋጥሯል፤ የተሰባበሩት ቱቦዎቿ የነዋሪዎቿን ፈተና ከማብዛት በቀር በከተማዋ የክፍለ ዘመናት ታሪክ ከ30 ሰዎች በላይ የሥራ ዕድል የሚፈጥር አንድም ድርጅት የለም፡፡
በ1770ዎቹ ገደማ ከተመሠረቱ ጥንታዊ ከተሞች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ የየጁ እና የጎንደር ክፍለ ሀገርን አጣምረው ይገዙ የነበሩት ራስ አሊ እንደቆረቆሯት ይነገራል፡፡ ስያሜዋ ጋር በተያያዘ ታላቁ ራስ አሊ ቤተ መንግሥታቸውን ካሠሩት ገብርኤል ተራራ ላይ ሁነው በቀድሞ አዋጅ መንገሪያ በዛሬው ማክሰኞ ገበያ ላይ አንዳች ነጭ ነገር አዩ፡፡ በያኔው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ እና ብዙ ምንጮች በነበሩት አካባቢ ራስ አሊ አገልጋያቸውን የሚታየው ነጭ ነገር ምን እንደሆነ አይቶ እንዲመጣ ይልኩታል፡፡ አገልጋያቸውም የወላድ ልብሶች ተሰጥተው ማየቱን ይነግራቸዋል፡፡ ንጉሡም የአገልጋያቸውን መረጃ ሲያስረግጡ ማዶ ማዶ እያዩ ‹ወልዳ› ‹ያ!› በማለት እያመለከቱ እንደተናገሩና ለስያሜው መነሻ እንደሆነ ከከተማው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ራስ አሊ ገና በምሥረታዋ ጥለዋት ደብረ ታቦር ላይ ነግሠው ሲቀመጡ የወልዲያ ሕዝብ ልማትና ችሎቱ ሲርቅ ‹‹ማማው ደብረ ታቦር ደጋሌቱ የጁ፣ ወንጭፍ አጠረና ወፎቹ እህል ፈጁ›› በማለት የአስተዳድሩ ርቀት ከተማዋ እንዳታድግ ማድረጉን ለማሳየት ተቀኙ፡፡
የከተማ አስተዳድሩ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለምነው ጌጡ በወልዲያ ከተማ በበጀት ዓመቱ ከ4 ሺህ 800 በላይ ዜጎች ሥራ ፈላጊዎች ሆነው መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ጥረት የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው ለ1 ሺህ 200 ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው ‹‹በከተማዋ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ባለመኖራቸው መንግሥት ብቻ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተገድዷል›› ይላሉ፡፡ ባለሀብቶች በከተማዋ እንደ እቅዳቸው የሥራ ዕድል ያለመፍጠርና የኢንዱስትሪው አለመስፋፋት ለሥራ ዕድል ያልተመዘገቡ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች መንገድ ላይ እንዲቆሙ አስገድዷቸዋል ብለዋል፡፡ ወልዲያ ከተማ ጎንደር በር ከተባለ ቦታ ሥራ ፍለጋ መንገድ ዳር ከቆሙት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዜጎች መካከል አንዱ አቶ ሞገስ ተስፋየን አግኝተን ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹ሥራ ነው?›› ብለውኝ ሥራ ላሠራቸው እንዳልሆነ ስነግራቸው ለዕለት ጉርስ ቀጣሪ ፍለጋ ምላሽ ሳይሰጡኝ ሌላ ሠራተኛ ጠያቂ ለመፈለግ ዓይናቸውን ወደሌላ አማተሩ፤ ግን ማንም አልነበረም፡፡
ሁለት ልጆች አሏቸው፡፡ ደሳሳ ጎጇቸውን በየወሩ 350 ብር ካልከፈሉባት ‹ይልቀቁ› እንደሚባሉ ያውቃሉ፡፡ ወፍጮ በማስፈጨት እና እንጀራ በመጋገር ጎጇቸውን ለማቆም የምትታትረው ባለቤታቸው ሥራ አጥተው በተመለሱ ጊዜ ትልቅ መፅናኛቸው ናት፡፡ ሁል ጊዜ ሥራ መፈለግ ኑሯቸውን ሙሉ በሰቀቀን እና በትግል እንዲገፉ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ፡፡ ወልዲያ ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ባለመኖራቸው ሙያም ሆነ ቋሚ የሥራ ዘርፍ እንዳይኖራቸው ማድረጉን ከስደት ተሞክሯቸው ተነስተው ያዩትን ችግር ነግረውናል፡፡
የከተሞች መስፋፋት ሥልጣኔ የሚሆነው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እኩል ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ ‹‹ያለ ኢንዱስትሪ ግንባታ፤ ያለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የከተሞች መስፋፋት ለዜጎች የሥራ እድል እጦት እና ለኑሮ ውድነት ከማጋለጥ በዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የወሎ ውበት፣ ፍቅር እና ገርነት ፈተና ላይ የሚወድቁት እየተስፋፋ የመጣውን ከተሜነት የሥራ ዕድል የሚያስገኙ ኢንዱስትሪዎች ካልተቋቋሙ ነው›› ሲሉ የከተማው ነዋሪ አቶ አያሌው አማረ ተናግረዋል፡፡ በወልዲያ ከተማ ሁለት የኢንዱስትሪ መንደሮች አሉ፡፡ ሥራ ላይ ከዋለው ከአንዱ ብቻ 23 ፕሮጀክቶች ባለፉት ሰባት ዓመታት ፈቃድ ወስደው ሥራ ጀምረዋል፡፡
ከኢንዱስትሪ መንደር ውጭ ደግሞ አራት አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሥራ የጀመሩት 5 ብቻ ናቸው፡፡ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡት የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ቢኖራቸውም እስካሁን የፈጠሩት ግን ለ263 ዜጎች ብቻ መሆኑን የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨሰትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድኖ ታረቀ ተናግረዋል፡፡ አቶ አድኖ እንዳሉት ይህም የከተማዋን የሥራ ፈላጊዎች ችግር እየፈታ ባለመሆኑ ድጋፍ ተደርጎላቸው በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉ ሦስት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ቦታ በመቀማት አቅም ላላቸው ሲሰጥ፤ አምስት ለሚሆኑት ደግሞ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡
‹‹ከወልዲያ ከተማ ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን ያለመገንባት ችግሮች የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ እና ከባለሀብቶች ጋር ተቃራርቦ የመሥራት ችግሮች ናቸው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በከተማዋ በሥራ አጦች ፍላጎት ልክ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲጥር የነበረው መንግሥት ብቻ በመሆኑ በቂ እንዳልነበርም አስታውቀዋል፡፡ በሕጉ መሠረት የጠየቁ ባለሀብቶችም ወደ ኢንዱስትሪው ለመግባት ፍላጎት አለማሳየታቸው ችግር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሥራ ዕድል ምንጩ መንግሥት ብቻ እንዳይሆን ለአልሚ ባለሀብቶች በራችን ክፍት ነው›› ብለዋል አቶ አድኖ፡፡ በቀጣይ የዜጎችን ጥያቄ ለመመለስ ባለሀብቶች በጋራ እና በተናጠል በአገልግሎት እና አምራች ዘርፎች እንዲሠማሩ 350 ሄክታር ነፃ መሬት እና 33 ሄክታር ካሳ የተከፈለበት መሠረተ ልማቱ የተሟላ ቦታ ማዘጋጀታቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ 25 የሚሆኑ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ለመሠማራት ፍላጎት በማሳየታቸው የከተማዋን የሥራ ዕድል የሚፈቱ ተስፋዎች እንደሚሆኑ የሚያምኑት ኃላፊው የአዋጭነት ዕቅዳቸውን በአጭር ጊዜ በመገምገም በጨረታም ሆነ በምደባ ቦታ እንዲያገኙ እንደሚወሰንም ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ